ወጣቶች በጋራ ራዕይ በመመራት ለሀገር ግንባታ ያላቸውን ቁልፍ ሚና ሊወጡ ይገባል - አቶ አደም ፋራህ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 29/2017(ኢዜአ)፦ ወጣቶች በጋራ ራዕይ በመመራት ለሀገር ግንባታ ያላቸውን ቁልፍ ሚና እንዲወጡ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊ እና የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ ጥሪ አቀረቡ።

”ወጣቶች በሀገርና በሀገረ-መንግሥት ግንባታ ውስጥ ያላቸው ሚና” በሚል ርዕስ በተከታታይ ሲካሄድ የቆየው የውይይት መድረክ ማጠቃለያ የሰላም ሚኒስቴር ከብልጽግና ወጣቶች ክንፍ ጋር በመተባበር “ሀገሬን እገነባለሁ ኃላፊነቴንም እወጣለሁ” በሚል መሪ ሃሳብ እየተካሄደ ይገኛል።


 

በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊ እና የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ በመድረኩ እንደተናገሩት ኢትዮጵያ በምጣኔ ሃብት፣ በፖለቲካ፣ በማህበራዊና በዲፕሎማሲ ሁለንተናዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ ራዕይ አስቀምጣ እየሰራች ትገኛለች።

ኢትዮጵያ ይህንን ራዕይ ለማሳካት አሻጋሪ ዕሳቤዎችና የረጅም ጊዜ ዕቅድ ይዛ ተግባራትን እያከናወነች ትገኛለች ብለዋል።

ኢትዮጵያ ሰፊ የህዝብ ቁጥር ያላት ከዚህ ውስጥም አብዛኛው ወጣት እንዲሁም የተፈጥሮ ሃብቶቿ ካሏት ሰፊ እድሎች መካከል መሆናቸውን አንስተዋል።

መንግስት ወጣቱን ተጠቃሚ ለማድረግና በምጣኔ ሃብት እድገት ውስጥ በማሳተፍ የወጣቱን ህልም የሚያለመልሙ እቅዶችን በመተግበር ዘርፈ ብዙ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል ብለዋል።

ወጣቶች የግል ራዕያቸውን ከሀገር ራዕይ ጋር በማጣጣምና በማዘጋጀት ህብረ ብሔራዊ አንድነትን ለማጠናከር መስራት ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት።

በተለይም አንድነትን የሚያጠናክሩ፣ መቻቻልን የሚያጎለብቱ እንዲሁም በዘላቂ ሰላም ግንባታ ላይ በስፋት መስራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

በዚህም ወጣቶች በጋራ ራዕይ በመመራት ለሀገር ግንባታ ያላቸውን ቁልፍ ሚና ሊወጡ እንደሚገባ ጠቁመው መንግስት ሁኔታዎችን በማመቻቸት ሚናውን አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።


 

የሰላም ሚኒስትር መሐመድ እድሪስ በበኩላቸው፤ ወጣቶች ኢትዮጵያ በተለያየ ወቅት የገጠሟትን ፈተናዎች ለማሻገር የተጫወቱት ሚና ጉልህ መሆኑን አንስተዋል።

የብልጽግና ፓርቲ ወጣቶች ክንፍ ፕሬዝዳንት አክሊሉ ታደሰ የተካሔዱ ውይይቶች በፖለቲካዊ፣ ምጣኔ ሃብትና ማህበራዊ ዘርፎች የወጣቱን ተጠቃሚነት በማረጋገጥ እንዲሁም በሚስተዋሉ ክፍተቶች ላይ ሰፊ ውይይት መደረጉን ገልጸዋል።

በተመሳሳይ በዘላቂ ሰላም ግንባታ ጥልቅ ውይይት የተደረገበትና ቀጣይ የትኩረት መስኮች ላይ መግባባት የተደረሰበት እንደሆነም ገልጸዋል።

በውይይት መድረኩ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት፣ የፌዴራልና የክልል መንግስታት ከፍተኛ አመራሮች፣ የክልልና ከተማ አስተዳደር ወጣት ተወካዮች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም