በዞኑ በተለያየ ምክንያት በተራቆተ 5 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ችግኝ እየተተከለ ነው

ነገሌ ቦረና፤ ሰኔ 29/2017 (ኢዜአ) በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ቦረና ዞን በተለያየ ምክንያት በተራቆተ 5 ሺህ ሄክታር  መሬት ላይ ችግኝ እየተተከለ መሆኑን የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት ገለጸ።

በጽህፈት ቤቱ የተፈጥሮ ሀብት ቡድን መሪ አቶ አልዬ አረባ  ለኢዜአ እንደገለፁት የችግኝ ተከላው እየተከናወነ የሚገኘው በተፈጥሯዊ እና በሰው ሰራሽ ምክንያት በተራቆተ 5 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ነው፡፡

በዞኑ ባለው የአየር ጸባይ ምክንያት ተከላው የተጀመረው ከመጋቢት አጋማሽ ጀምሮ መሆኑን ተናግረዋል።


 

 

የችግኝ ተከላው የተራቆተ መሬት እንዲለመልም ከማድረግ ባሻገር የድርቅ ተጋላጭነትን በዘላቂነት መቋቋምን ታሳቢ ባደረገ መልኩ እየተከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ዘንድሮ እየተተከሉ ከሚገኙ ችግኞች መካከል የደን፣ የጥላ ዛፍ፣ የእንስሳት መኖ እንዲሁም ከፍራፍሬ ችግኞች ማንጎ፣ ሙዝና ዘይቱን ዋና ዋና ዎቹ እንደሆኑ አመልክተዋል፡፡


 

የችግኝ ተከላው የዞኑን ነዋሪዎችና በጎ ፈቃደኞችን ባሳተፈ መልኩ እየተከናወነ ሲሆን የተያዘው እቅድ እስከሚሳካ ድረስ ተከላው በትኩረት እንደሚከናወንም አስረድተዋል።

በዞኑ በበጋ ወራት ዘንድሮ በ99 ተፋሰሶች ውስጥ 63 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የአፈርና ውሀ ጥበቃ ስራ መከናወኑን አስታውሰዋል፡፡

የተፋሰስ ልማት ስራው ዓላማ በዋናነት ድርቅና የአካባቢ መራቆትን ከመከላከል ባለፈ በዘላቂ ልማት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ታሳቢ ያደረገ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

የአረንጓዴ አሻራ እና የችግኝ ተከላ ስራም የተፋሰስ ልማቱን ጭምር በእጽዋት ለማልበስ ታቅዶ የተከናወነ ነው ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም