መገናኛ ብዙሃን ፍጥነትና ፈጠራ የታከለባቸው የይዘት ሥራዎች ላይ አተኩረው ሊሰሩ ይገባል -አፈ ጉባዔ ታገሰ ጫፎ - ኢዜአ አማርኛ
መገናኛ ብዙሃን ፍጥነትና ፈጠራ የታከለባቸው የይዘት ሥራዎች ላይ አተኩረው ሊሰሩ ይገባል -አፈ ጉባዔ ታገሰ ጫፎ

አዲስ አበባ፣ሰኔ 28/2017 (ኢዜአ)፦የድህረ-እውነት ዘመን ተግዳሮቶችን ለመሻገር መገናኛ ብዙሃን ፍጥነትና ፈጠራ የታከለባቸው የይዘት ሥራዎች ላይ አተኩረው ሊሰሩ እንደሚገባ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ ታገሰ ጫፎ አስገነዘቡ።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተጠሪ የዴሞክራሲ ተቋማት የሪፎርም ሥራቸውን በተመለከተ የጋራ ምክክር መድረክ አካሂደዋል።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ በወቅቱ እንደገለጹት፤ ምክር ቤቱ ክትትልና ድጋፍ በሚያደርግላቸው መገናኛ ብዙሃን ያሉ ችግሮችን በመጋፈጥ የተሻለ የይዘት ስራ እየሰሩ ናቸው።
በመድረኩ የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት የሥራ ሃላፊዎች የሪፎርም ሥራዎችን አፈጻጸም ሪፖርት አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትን ተቋማዊ ሪፎርም አስመልክቶ ዋና ሥራ አስፈፃሚው አቶ ሠይፈ ደርቤ ባቀረቡት ሪፖርት እንደገለጹት፤ ኢዜአ ብሄራዊ ጥቅምን የማስጠበቅና ብሄራዊ መግባባትን የመፍጠር ተልዕኮውን በአግባቡ ለመወጣት የተለያዩ ተግባራትን አከናውኗል።
የኢዜአ ማቋቋሚያ አዋጅ በምክር ቤቱ መፅደቁን ተከትሎ በሰው ሃይል፣ በአሰራርና አደረጃጀት ለይቶ ወደ ሥራ መግባቱንም አስታውሰዋል።
ኢዜአ በአገር ውስጥና በውጭ ቋንቋዎች የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም የሚያስጠብቁና የአገር ገፅታ የሚገነቡ ጠንካራ የይዘት ስራዎችን እያሰራጨ መሆኑንም ነው ያብራሩት።
ተቋሙ በዲጂታል ሚዲያውም የኢትዮጵያን እውነትና መሻት የሚያንፀባርቁ ይዘቶችን ለአገር ውስጥና ለውጭ መገናኛ ብዙሃን ተደራሽ እያደረገ ነው ብለዋል።
በአሁን ወቅትም በአምስት የአገር ውስጥና በሶስት የውጭ ቋንቋዎች የኢትዮጵያን ፍላጎት የሚያሳዩና ገፅታ የሚገነቡ መረጃዎችን ተደራሽ እየተደረገ ነው ብለዋል።
ኢዜአ የተሰጠውን አገራዊ ተልዕኮ መወጣት የሚያስችለውን የህግና አሰራር ክፍተቶች ከመሙላት አኳያ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ላደረገውና እያደረገ ስላለው ድጋፍም አመስግነዋል።
የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢቢሲ) ዋና ሥራ አስፈጻሚ ጌትነት ታደሰ በበኩላቸው፤ ኢቢሲ ችግሮችን በጥልቅ በመለየት ከአገራዊ ለውጡ በኋላ የይዘት፣ የገበያ፣ የቴክኖሎጂና የኮርፖሬት ሪፎርሞችን በማካሄድ ወደ ሥራ መግባቱን ተናግረዋል።
በዚህም የፈጠራ ዘርፍ በማቋቋምና በክልል ያሉ ሃብቶችን ጥቅም ላይ ለማዋል የጀመራቸው ስራዎች ውጤት እያመጡ መሆኑን ነው የተናገሩት።
ኢቢሲ ባሉት የቴሌቪዥን፣ የሬድዮና የዲጂታል አማራጮች ገዥ ትርክትን የሚያሰርፁ ጠንካራ የይዘት ስራዎችን እየሰራ መሆኑንም አንስተዋል።
የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ መሳፍንት ተፈራ በበኩላቸው፤ የዲጂታል ሚዲያው መስፋፋትን ተከትሎ በህትመት ውጤቶች ላይ የተጋረጡ ፈተናዎችን ለመሻገር የተለያዩ ሪፎርሞች መደረጋቸውን ነው ያብራሩት።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ እንደገለጹት፤ በድህረ እውነት ዘመን የሀሰተኛ እና የጥላቻ ንግግር ላይ ያሉ ተግዳሮቶችን ለመፍታት በዕውቀትና እውነት ላይ ተመስርቶ የሚሰራ መገናኛ ብዙሃን ያስፈልጋል።
ምክር ቤቱ ክትትልና ድጋፍ በሚያደርግላቸው መገናኛ ብዙሃን ያሉ ችግሮችን በመጋፈጥ የተሻለ የይዘት ስራ ለመስራት እያደረጉት ያሉውን ጥረት ያደነቁት አፈ ጉባዔው፤ የድህረ-እውነት ዘመን ተግዳሮቶችን ለመሻገር መገናኛ ብዙሃኑ ፍጥነትና ፈጠራ ለታከለባቸው የይዘት ሥራዎች ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩ አስገንዝበዋል።
ምክር ቤቱም ለዴሞክራሲ ተቋማቱ ውጤታማነት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ነው የገለጹት።
የምክር ቤቱ ምክትል አፈ ጉባኤ ሎሚ በዶ በበኩላቸው፤ ከአገራዊ ለውጡ በኋላ መገናኛ ብዙሃን ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ያለውን ቁልፍ ሚና በመረዳት ልዩ ትኩረት መሰጠቱን አመልክተዋል።
በድህረ እውነት ዘመን የመገናኛ ብዙሃን ገዥ ትርክትን ለማስረፅ የጀመሩትን ሥራ አጠናክረው እንዲቀጥሉ አሳስበዋል።
ኢዜአ ከተመሰረተ ረጅም ዓመታት ቢያስቆጥርም በየጊዜው የሚያጋጥሙትን ፈተናዎች እየተሻገረ አሁን የደረሰበት ደረጃ በመድረሱ አድንቀዋል።
በምክር ቤቱ የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ እውነቱ አለነ በመገናኛ ብዙሃን ላይ የነበሩ የአሰራርና አደረጃጀት ችግሮች በሂደት እየተፈቱ መምጣታቸውን ነው ያነሱት።
ኢዜአ በርካታ ውጣ ውረዶችን አልፎ አስተማማኝ የዜና ምንጭ ለመሆን እያደረገ ያለው ጥረት የሚደነቅ መሆኑንም ተናግረዋል።