ከአገራዊ ሪፎርሙ ወዲህ ለ174 መገናኛ ብዙሃን ህጋዊ ፍቃድ ተሰጥቷል - ኢዜአ አማርኛ
ከአገራዊ ሪፎርሙ ወዲህ ለ174 መገናኛ ብዙሃን ህጋዊ ፍቃድ ተሰጥቷል

አዲስ አበባ፣ሰኔ 28/2017 (ኢዜአ)፦ከአገራዊ ሪፎርሙ ወዲህ ለ174 መገናኛ ብዙሃን ፍቃድ መስጠቱን የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን አስታወቀ።
ባለስልጣኑ የተቋማዊ ሪፎርም ስራዎችን አፈጻጸም ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላትና የዲሞክራሲያዊ ተቋማት የጋራ መድረክ ላይ ሪፖርት አቅርቧል።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዮናታን ተስፋዬ እንደገለጹት ባለስልጣኑ ከአገራዊ ለውጡ በኋላ ሀሳብን በነፃነት የመግለፅና የሚዲያ ነፃነትን የሚያረጋግጡ ሥራዎችን ሰርቷል።
የጥላቻ ንግግርና ሀሰተኛ መረጃን ለመከላከል በአዋጅ የተሰጠውን ስልጣንና ኃላፊነት ለመወጣት በርካታ ተግባራትን ማከናወኑን አብራርተዋል።
ባለስልጣኑ የተሰጠውን ተልዕኮ በአግባቡ መወጣት የሚያስችል የህግ ማሻሻያ ማድረጉንም እንዲሁ።
ከለውጡ በፊት በዘርፉ የሚሰሩ የሙያና ሲቪክ ማህበራት ከስድስት የማይበልጡ እንደነበሩ አንስተው፤ አሁን ላይ ለውጡን ተከትሎ 38 ማህበራትና አደረጃጀቶች ወደ ስራ መግባታቸውንም ነው ያብራሩት።
ከአገራዊ ለውጡ በኋላ በትምህርት በማህበረሰብ ሬዲዮ፣ በሃይማኖት፣ በቴሌቪዥንና በሬዲዮ እንዲሁም በዲጂታል ሚዲያ ላይ ፍቃድ ወስደው የሚሰሩ መገናኛ ብዙሃን ቁጥር መጨመሩንም ነው የገለጹት።
በዚህም ከአገራዊ ለውጡ በኋላ 174 አዳዲስ መገናኛ ብዙሃን ከባለስልጣኑ ፍቃድ ወስደው ወደ ስራ መግባታቸውን አብራርተዋል።
የመገናኛ ብዙሃኑ የቋንቋ ተደራሽነትም ከነበረበት 39 አሁን ላይ ወደ 63 ከፍ ማለቱን አመልክተዋል።