መንግስት ለስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች መገንቢያ ከፍተኛ ሀብት ከመመደብ ጀምሮ ለዘርፉ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቷል

ባሕርዳር፤ ሰኔ 28/2017(ኢዜአ)፡- መንግስት ለስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች መገንቢያና እድሳት ከፍተኛ ሀብት ከመመደብ ጀምር ለስፖርቱ ዘርፍ  ከፍተኛ   ትኩረት  መስጠቱን  የባህልና ስፖርት ሚኒስትር  ሸዊት ሻንካ ገለጹ።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት  የሚያዘጋጀው  ስለኢትዮጵያ ምዕራፍ ሁለት፣7ኛ መድረክ  "ስፖርት ለአሸናፊ  ሀገር " በሚል መሪ ሀሳብ  ዛሬ በባሕርዳር  አለም አቀፍ ስታዲዮም  ተካሂዷል። 

በመድረኩ ማጠቃለያ የተገኙት የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ አረጋ ከበደ  ከባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ ጋር በባሕር ዳር አለም አቀፍ  ስታዲዮም ችግኝ በመትከል አረንጓዴ አሻራቸውን አኑረዋል።


 


 

ሚኒስትሯ  ሸዊት ሻንካ በመድረኩ  ማጠቃለያ እንዳመለከቱት፤ እንደ ሀገር በሌሎች ዘርፎች ላይ የታቀዱ ዕቅዶችን ለማሳካት  ጠንካራና በስፖርት የዳበረ ጤናማ ማህበረሰብ ለመገንባት ስፖርት ያለውን አስተዋጽኦና  ሚና በመገንዘብ   መንግስት ለዘርፉ ልማት ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቷል።


 

ለዚህም ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)  ጀምሮ ከፍተኛ  የሀገሪቱ የመንግስት ስራ ኃላፊዎች  በሄዱበት አካባቢ የስፖርት ማዘውተሪያ  ስፍራዎችን በማበረታታት  ድጋፍ እየሰጡ መሆኑን አንስተዋል።

ስፖርት በተባበረ ክንድ ሀገርን ለመገንባትና ህብረብሔራዊ አንድነትን ለማጠናከር የሚያስችል እንደሆነ የገለጹት ሚኒስትሯ፤  ይህንን ከግምት ያስገቡ ተግባራት በመከናወን ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

ለዚህም መንግስት የስፖርትን  ዘርፈ ብዙ ፋይዳ ከግምት ያስገባ  ከታች ጀምሮ እስከ ፌደራል ድረስ  ከፍተኛ የሆነ ሀብት በመመደብ  ስፖርታዊ ውድድሮች እንዲጠናከሩ፣  የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች እንዲገነቡና እድሳት እንዲያገኙ በማድረግ ላይ መሆኑን  ገልጸዋል።

"አሸናፊ ስነ-ልቦናና ሀገረ መንግስት ግንባታ"በሚል ርዕስ  የመወያያ ጽሁፍ ያቀረቡት የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት  ሚኒስትር ዴኤታ ተስፋሁን ጎበዛይ በበኩላቸው እንዳሉት፤ እንደመንግስት የስፖርት  መሰረተ ልማት በመገንባት ከፍተኛ የሆነ ትኩረት ሰጥቷል።


 

ስፖርት የስፖርታዊ እንቅስቃሴ ብቻ ሳይሆን የሀገር መገንቢያ ኃይል አንዱ ትልቅ መሳሪያ  ነው ተብሎ ተለይቶ እየተሰራበት ይገኛል ብለዋል።

የስፖርቱ ማህበረሰብ ለሀገረ መንግስት ግንባታ ሚና እንዲኖረው    የተደራጀ ስራ መከናወን እንዳለበት አመልክተዋል። 

ለዚህም ስራዎች በመከናወን ላይ መሆናቸውን አንስተው፤ ለዘርፉ እድገት ሚዲያውን ጨምሮ  ሁሉም አካል የድርሻውን መወጣት እንዳለበት አስገንዝበዋል።

ኢንስትራክተር አብረሃም መብራቱ በበኩላቸው እንዳሉት፤  ኢትዮጵያ  በአለም ኦሎምፒክ፣ በፊፋና በካፍ  ተሰሚነት ያላቸው  ትልልቅ ሰዎችን ያፈራች ሀገር ናት።


 

አሁን ላይ የክለቦች አወቃቀር  ዘመናዊና ወቅታዊ ያለመሆንና የመልካም አስተዳደር ክፍተት  እንዲሁም  የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች አለም አቀፍ ደረጃቸውን  የጠበቀ አለመሆን  የዘርፉ መሰናክሎች መሆናቸውን አንስተዋል።

እንደ ሀገር ለስፖርቱ  በፖሊሲ ደረጃ የተሰጠው ትኩረት ከሌሎች አገራት የተሻለና ሊያሰራ የሚችል እንደሆነም አብራርተዋል። 

በመድረኩ ማጠቃለያ የተገኙት የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ አረጋ ከበደ  ከባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ ጋር በባሕር ዳር አለም አቀፍ  ስታዲዮም ችግኝ በመትከል አረንጓዴ አሻራቸውን አኑረዋል።

በመድረኩ የፌደራልና የክልል ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ፣ የስፖርት ባለሙያዎች፣አሰልጣኞችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት የተሳተፉ ሲሆን፤  ስፖርትን የተመለከተ አውደ ርዕይም  ለእይታ ቀርቧል። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም