በማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አገልግሎት 63 ሚሊዮን ዜጎች ተጠቃሚ ሆነዋል

አዲስ አበባ፣ሰኔ 28/2017 (ኢዜአ)፦በ2017 በጀት ዓመት የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን አገልግሎት ተጠቃሚ ዜጎች ቁጥር 63 ሚሊዮን መድረሱን የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ ገለፁ።

የሰቆጣ ቃል ኪዳን፣ የምግብና ሥርዓት ምግብ እንዲሁም የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አገልግሎት የ2017 በጀት ዓመት አፈፃፀም ግምገማ መድረክ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ እና ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት አመራሮች በተገኙበት በአዲስ አበባ ተካሂዷል።


 

የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ በዚሁ ወቅት፥ ስርዓተ ምግብን ማሻሻል ጤናማና አምራች ትውልድ ለማፍራት ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።

የምግብና ስርዓተ ምግብ የ10 ዓመት ስትራቴጂና የሰቆጣ ቃልኪዳን ማስፋፊያ ምዕራፍ ባለፉት አራት ዓመታት ተስፋ ሰጪ በሆነ መንገድ እየተተገበሩ መሆኑን አንስተዋል።

በሰቆጣ ቃልኪዳን በማስፋፋት ምዕራፍ ትግበራው በ2017 በጀት ዓመት በ334 ወረዳዎች መተግበሩን ተናግረዋል።

በዚህም በሚሊዮን የሚቆጠሩ የሚያጠቡና ነፍሰጡር እናቶች እንዲሁም ህጻናት ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የሰቆጣ ቃል ኪዳን አበርክቶን ለማሳደግ በ2018 ዓ.ም የሚተገበርባቸውን ወረዳዎች 520 ለማድረስ ዝግጅት እየተደረገ ነው ብለዋል። 

በቃልኪዳኑ መሠረት በ2022 ዓ.ም መቀንጨርን ዜሮ ለማድረግ የምግብና ስርዓተ ምግብ ተግባራትን ሽፋን ማሳደግ እንዲሁም በቂ ሀብት መመደብ ላይ በሁሉም ክልሎችና በከተማ አስተዳደሮች ተመሳሳይ ስራዎችን ማከናወን እንደሚገባው አንስተዋል።

ሥርዓተ ምግብን ለማሻሻልና ሀገራዊ የጤና ግቦችን ለማሳካት የሌማት ትሩፋት፣ የአረንጓዴ አሻራ እና ሌሎች ኢኒሼቲቮች ወሳኝ ሚና እያበረከቱ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

በሌላ በኩል የሁሉን አቀፍ የጤና ተደራሽነትን እውን ለማድረግ የማይበገር የጤና ስርዓት በመገንባትና የጤና መሰረተ ልማትን በማስፋት የጤና አገልግሎት ሽፋንን ከ95 በመቶ በላይ ማድረስ ተችሏል ነው ያሉት።

የጤና መድህን ስትራቴጂ መክፈል የማይችሉ ዜጎችን የጤና ዋስትና ለማሳደግ የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አገልግሎት እየተተገበረ መሆኑን ገልጸዋል።

የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አገልግሎት ሽፋን በ2017 በጀት ዓመት ወደ 1ሺህ 195 ወረዳዎች ተደራሽ መደረጉን ተናግረዋል።

በዚህም 63 ሚሊዮን ዜጎች በማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን መርሃግብር ተጠቃሚ እየሆኑ  እንደሚገኙ አንስተዋል።

ይህም የተሳካው በሁሉም ክልሎች የመክፈል አቅምን መሰረት ያደረገ አሰራር በመተግበሩ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም