የገጠር መሬት ይዞታ ማረጋገጫ ደብተር መሬታችንን ለማልማት ይገጥመን የነበረን የፋይናንስ ብድር ችግር ፈቶልናል- አርሶ አደሮች - ኢዜአ አማርኛ
የገጠር መሬት ይዞታ ማረጋገጫ ደብተር መሬታችንን ለማልማት ይገጥመን የነበረን የፋይናንስ ብድር ችግር ፈቶልናል- አርሶ አደሮች

ወላይታ ሶዶ፣ ሰኔ 28/2017 (ኢዜአ)፦የገጠር መሬት ይዞታ ማረጋገጫ ደብተር ማግኘታቸው መሬታቸውን ለማልማት ይገጥማቸው የነበረን የፋይናንስ ብድር ችግር ለመፍታት ማስቻሉን በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አርሶ አደሮች ገለጹ።
በክልሉ የገጠር መሬት አስተዳደር እና አጠቃቀም ኤጀንሲ ''መሬት የሀብት ሁሉ ምንጭ ነው'' በሚል መሪ ሀሳብ የ2017 በጀት ዓመት አፈጻጸም እና የ2018 ዓ.ም ዕቅድ ላይ ያዘጋጀው ኮንፍረንስ በወላይታ ሶዶ ከተማ ተካሂዷል።
ኢዜአ ካነጋገራቸው የኮንፈረንሱ ተሳታፊዎች መካከል የጌዴኦ ዞን አርሶ አደር አስማማው እንዳሉት የመሬት ይዞታ ማረጋገጫ ደብተር ማግኘታቸው መሬታቸውን በአግባቡ አልምተው ተጠቃሚነታቸውን ለመሳደግ አግዟቸዋል።
በተለይ ከዚህ ቀደም የቡና ልማት ሥራቸውን ለማስፋፋት ይገጥማቸው የነበረን የገንዘብ ችግር እንደፈታላቸው ነው የገለጹት።
ከወላይታ ዞን የመጡት አርሶ አደር ተስፋዬ ቱካ በበኩላቸው የይዞታ ማረጋገጫው ከዚህ ቀደም ከእርሻ መሬት ወሰን ጋር በተያያዘ ይገጥማቸው የነበረን ውዝግብ ለመፍታት እንዳስቻላቸው ገልጸዋል።
የመሬት ልኬት ምስክር ወረቀት ካገኙ ወዲህ በወሰዱት ብድር የግብርና ሥራቸውን በማስፋፋት ከራሳቸው ባለፈ ለ12 ወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠራቸውን ተናግረዋል።
የመሬት አስተዳደር ሥርዓቱን በማዘመን የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በተሰራው ሥራ 386 ሺህ አርሶ አደሮችን ወደ ቋት ማስገባት ተችሏል ያሉት ደግሞ የወላይታ ዞን መሬት አስተዳደር እና አጠቃቀም ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አስፋው ሴታ ናቸው።
አርሶ አደሮች የመሬት ይዞታ ማረጋገጫ ደብተራቸውን ዋስትና በማስያዝ ከብድር አቅራቢ ተቋማት ገንዘብ በመበደር የግብርና ልማት ሥራቸውን እያስፋፉ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በክልሉ ግብርና ቢሮ የገጠር መሬት አስተዳደር እና አጠቃቀም ኤጄንሲ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ኖህ ታደለ በበኩላቸው የገጠር መሬት አያያዝና አጠቃቀምን ለማሻሻል የተጀመረው ሥራ ህገወጥ የመሬት ወረራን ለመከላከል፣ የመሬት አስተዳደር ሥርዓቱን ለማዘመንና ለወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ማገዙን ጠቁመዋል።
በክልሉ የ2ኛ ደረጃ መሬት ልኬት በተካሄደባቸው 48 ወረዳዎች ከ2 ሚሊዮን 48 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች የገጠር መሬት ይዞታ ማረጋገጫ ደብተር አግኝተዋል።
ተግባሩን በማጠናከር በቀጣይም በ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ማሳዎች ላይ ልኬትና ምዝገባ ለማካሄድ መታቀዱን ጠቁመዋል።
አርሶ አደሮች የማረጋገጫ ደብተሩን በመጠቀም ከፋይናንስ ተቋማት ገንዘብ መበደር እንዲችሉ በመደረጉ የበርካቶች ኑሮ እየተሻሻለ መምጣቱንም ዋና ሥራ አስኪያጁ አክለዋል።
በመድረኩ የክልሉ መንግስት የሥራ ሃላፊዎችና ሌሎች ባለድርሻዎች ተገኝተዋል።