በስርዓተ ምግብ፣ በሰቆጣ ቃልኪዳንና የማህበረሰብ ጤና መድህን አገልግሎት ተጨባጭ ውጤቶች ተመዝግበዋል - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ - ኢዜአ አማርኛ
በስርዓተ ምግብ፣ በሰቆጣ ቃልኪዳንና የማህበረሰብ ጤና መድህን አገልግሎት ተጨባጭ ውጤቶች ተመዝግበዋል - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 28/2017(ኢዜአ)፦በስርዓተ ምግብ፣ በሰቆጣ ቃልኪዳንና የማህበረሰብ ጤና መድህን አገልግሎት ተጨባጭ ውጤቶች መመዝገባቸውን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።
መርሃ-ግብሮቹ የአመራሩ ቁርጠኝነትና የማህበረሰቡ የባለቤትነት ተሳትፎ ስኬት ማሳያዎች እንዲሁም ለሌሎች ፕሮግራሞች ትግበራ ልምድ የሚወሰድባቸው ሀገር በቀል መፍትሔዎች መሆናቸውንም ገልጸዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት የሰቆጣ ቃል ኪዳን፣ የምግብና ሥርዓት ምግብ እንዲሁም የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድኅን የ2017 በጀት ዓመት አፈፃፀም ግምገማ መድረክ ላይ ነው።
መቀንጨርንና ሌሎች የስርዓተ-ምግብ ችግሮችን ለመቅረፍ ማሕበረሰቡን ማዕከል ያደረጉ ተግባራትን ማስፋፋት ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።
በምግብ እና ስርዓተ ምግብ ስትራቴጂ እና በሰቆጣ ቃል ኪዳን የተቀመጡ ግቦች ሊሳኩ የሚችሉት የማሕበረሰብ ንቅናቄ በመፍጠር የችግሩ መፍትሔ ሰጪ በማድረግ ነው ብለዋል፡፡
ከዚህ አንጻር በሰቆጣ ቃል ኪዳን የማስፋፋት ምዕራፍ ትግበራ ህዝቡን ባለቤት በማድረግ፣ ሀብትና ጉልበትን በአግባቡ በመጠቀም ውጤታማ ተግባራት መከናወናቸውን ጠቅሰዋል።
የስርዓተ ምግብ ችግሮችን በመለየት በራስ አቅም መፍታት የሚያስችሉ አካባቢያዊ ፈጠራዎችን በወረዳዎች እና ቀበሌዎች መተግበር መቻሉ እየመጣ ላለው ለውጥ ቁልፍ አስተዋጽኦ አለው ብለዋል፡፡
የሰቆጣ ቃል ኪዳን ትግበራ ወሳኝ ምዕራፍ ላይ መድረሱን ጠቅሰው፥ የማስፋፋት ምዕራፍ በመጪው ዓመት እንደሚጠናቀቅም ገልጸዋል።
በ15 ዓመታት ፍኖተካርታው መሠረትም ወደ ቀጣዩ የ5 ዓመታት የማስፋት ምዕራፍ ሽግግር ቁልፍ ተግባራትን ማከናወን ይገባል ነው ያሉት፡፡
በቤተሰብ ደረጃም ለውጥ ማምጣት የሚያስችሉ አካሔዶችን መለየትና ውጤት ሊያመጡ የቻሉና አዋጪ ፈጠራዎችን ማስፋፋት እንደሚገባ አስረድተዋል።
በጤናው ዘርፍም የጥራት ደረጃውን የጠበቀ የጤና አገልግሎት ለሁሉም ዜጎች በፍትሃዊነት ተደራሽ ለማድረግ ሁሉን አቀፍ የጤና ሽፋን ግብን ለማሳካት የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድኅን ፕሮግራም እየተተገበረ መሆኑን አንስተዋል።
በ2017 በጀት ዓመት የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድኅን ትግበራ በርካታ ዜጎች የጤና መድኅን ሽፋን ማግኘታቸውንም አንስተዋል።
የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድኅን ፕሮግራም የህክምና ወጪ ስጋትን በመቅረፍ የዜጎችን የኑሮና የጤና ሁኔታ በማሻሻል ቁልፍ ሚና እየተጫወተ መሆኑን ገልጸዋል።
ከምግብ እና ስርዓተ ምግብ ስትራቴጂ እንዲሁም የሰቆጣ ቃል ኪዳን ትግበራን ለማፋጠን በቀጣይም ተቋማዊና ማህበረሰባዊ ተግባራትን ማሳለጥ እንደሚገባ አፅንኦት ሰጥተዋል።