በክረምቱ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ሁሉም በንቃት በመሳተፍ አሻራውን ሊያኖር ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
በክረምቱ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ሁሉም በንቃት በመሳተፍ አሻራውን ሊያኖር ይገባል

ሶማሌ፤ ሰኔ 28/2017 (ኢዜአ)፡- በክረምቱ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ሁሉም በንቃት በመሳተፍ አሻራውን ሊያኖር ይገባል ሲሉ የሶማሌ ክልል ርእሰ መስተዳድር ሙስጠፌ ሙሁመድ ገለጹ።
የክልሉ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት እና አረንጓዴ አሻራ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ርእሰ መስተዳድሩ በተገኙበት በጅግጅጋ ከተማ ተካሂዷል።
በዚሁ መርሃ ግብር ላይ ንግግር ያደረጉት የሶማሌ ክልል ርእሰ መስተዳድር ሙስጠፌ ሙሁመድ፤ በክልሉ የአረንጓዴ አሻራ ልማትን ጨምሮ በተከናወኑ ዘርፈ ብዙ የልማት ስራዎች ውጤት እየተመዘገበ መሆኑን ገልጸዋል።
በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ባለፉት አመታት በተከናወኑ ስራዎች አካባቢን በመጠበቅና የምግብ ዋስትናን የማረጋገጥ ሂደት ስኬቶች መታየታቸውን አንስተዋል።
በመሆኑም በዘርፉ ልማት ዘንድሮም ዝግጅት መደረጉን ገልጸው በመርሃ ግብሩ ሁሉም በነቂስ በመሳተፍ አሻራውን እንዲያሳርፍ አስገንዝበዋል።
ከችግኝ ተከላ በተጨማሪ በክረምት በጎ ፈቃድ የአረጋውያንና አቅመ ደካሞችን ቤት በማደስና በመገንባት፣ በአካባቢ ጥበቃ፣በደም ልገሳ እና ሌሎችም መስኮች ነፃ አገልግሎቱ እንዲጠናከር አፅእኖት ሰጥተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የዘንድሮውን የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር ሰኔ 20 ቀን 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ በይፋ ማስጀመራቸው ይታወቃል።