በጎንደር እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ፕሮጀክቶች የከተማውን እድገት የሚያፋጥኑ ናቸው - ኢዜአ አማርኛ
በጎንደር እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ፕሮጀክቶች የከተማውን እድገት የሚያፋጥኑ ናቸው

ጎንደር፤ ሰኔ 28/2017(ኢዜአ)፡- በጎንደር እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ፕሮጀክቶች የከተማውን እድገት የሚያፋጥኑና የህዝቡንም የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያግዙ መሆናቸው ተገለጸ።
የአማራ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ ፣ የቋሚ ኮሚቴ አባላትና የክልሉ ከተማና መሠረተ ልማት ቢሮ የስራ ሃላፊዎች በጎንደር ከተማ እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ፕሮጀክቶች አፈጻጸምን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።
ዋና አፈጉባኤዋ ወይዘሮ ፋንቱ ተስፋዬ በጉብኝቱ ላይ እንደተናገሩት፤ በከተማው የሚካሄዱ የልማት ፕሮጀክቶች ላይ ተቀናጅቶ የመምራትና ጀምሮም የማጠናቀቅ ተቋማዊ አቅምና የአመራር ቁርጠኝነት የታየበት ነው።
በተለይ የከተማው የኮሪደር ልማት ስራ ሕዝቡን በባለቤትነት በማሳተፍ በአጭር ጊዜ ውስጥ የታየው ለውጥና የተመዘገበው ስኬት በሞዴልነት የሚወሰድ ነው ብለዋል።
የኮሪደር ልማት ስራው የከተማውን ውበት የገለጠ ምቹና ውብ የከተሜነት ገጽታን ያላበሰና ለዜጎችም የስራ እድል የፈጠረ መሆኑን አንስተዋል።
በተጨማሪም በከተማው እየተካሄደ ያለው የሴፍቲኔት መርሀ ግብር በከተሞች የሚታየውን ድህነት በመቀነስ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ወገኖች ጥሪት አፍርተው በአጭር ጊዜ ከድህነት የሚወጡበት ምቹ የኢኮኖሚ መደላድል የፈጠረ እንደሆነ መገንዘባቸውን ተናግረዋል።
በከተማው እየተገነባ ያለው ዘመናዊ የገበያ ማዕከል ከህገ ወጥ ደላሎች ነጻ በሆነ መንገድ አምራቹንና ሸማቹን በቀጥታ በማገናኘት ገበያውን በማረጋጋትና የኑሮ ውድነቱን በመቀነስ በኩል የጎላ ፋይዳ እንዳለውም ገልጸዋል።
የጠራ እቅድና ሀሳብን ወደ ተግባር ለመለወጥ የአመራሩና የሕብረተሰቡ የተቀናጀ እንቅስቃሴና ጥረት የሚበረታታ መሆኑን አስረድተዋል።
የክልሉ ምክር ቤት ሴቶች ህጻናት ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ አበራሽ ታደሰ በበኩላቸው፤ በከተማው እየተካሄደ የሚገኘው የሴፍቲኔት መርሀግብር የሴቶችን ኑሮና የስራ ባህል የቀየረ የገንዘብ ቁጠባ ባህላቸውንም ያሳደገ ነው ብለዋል።
በከተሞች እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ፕሮጀክቶች ለቴክኖሎጂ መስፋፋትና ለወጣቶች የስራ እድል ምቹ ሁኔታ እየፈጠሩ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የክልሉ ከተማና መሠረተ ልማት ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ ሱሌይማን እሸቱ ናቸው።
የጎንደር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ቻላቸው ዳኘው ፤ የተካሄደው ጉብኝት የከተማ አስተዳደሩ የልማት ፕሮጀክቶችን በፍጥነትና በጥራት እንዲያከናውን በቂ ግብአት የተገኘበት ነው ብለዋል።
በጉብኝቱ የኮሪደር ልማት ስራን ጨምሮ ዘመናዊ የገበያ ማዕከል ግንባታ፣ የከተማ ሴፍቲኔት ስራዎች ፣ የአረጋውያን የምገባ ማዕከልና የአረንጓዴ አሻራ ዝግጅት ምልከታ የተካሄደ ሲሆን፤ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር በጎሃ ተራራ ላይ ተከናውኗል።