በኦሮሚያ ክልል ያለውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም በርካታ ባለሃብቶች በኢንቨስትመንት ዘርፍ እየተሳተፉ ይገኛሉ - ኢዜአ አማርኛ
በኦሮሚያ ክልል ያለውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም በርካታ ባለሃብቶች በኢንቨስትመንት ዘርፍ እየተሳተፉ ይገኛሉ

ክልል፤ ሰኔ 28/2017(ኢዜአ)፡- በኦሮሚያ ክልል ያለውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም በርካታ የሀገር ውስጥና የውጭ ባለሃብቶች በኢንቨስትመንት ዘርፍ በመሳተፍ ላይ እንደሚገኙ ተገለጸ።
የሸገር አለም አቀፍ የኢንቨስትመንት አውደ ርዕይና ባዛር ዛሬ በአዲስ አለም አቀፍ ኮንቬንሽን ሴንተር ተከፍቷል።
ለሶስት ቀናት የሚቆየው አውደ ርዕዩ የሸገር ከተማን የኢንቨስትመንት አማራጮች ይበልጥ በማስተዋወቅ የሀገር ውስጥና የውጭ ባለሃብቶችን ለመሳብ ትልቅ ሚና እንዳለው የከተማ አስተዳደሩ ገልጿል ።
በአውደ ርዕዩ መክፈቻ ሥነ-ሥርዓት ላይ የጨፌ ኦሮሚያ አፈ-ጉባዔ ሳአዳ አብዱራህማን እና በኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት ማዕረግ የሸገር ከተማ ከንቲባ ተሾመ አዱኛ (ዶ/ር)ን ጨምሮ ሌሎችም የፌደራልና የክልል አመራሮች እንዲሁም ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተዋል።
በዚህ ወቅት የጨፌ ኦሮሚያ አፈ ጉባኤ ሳአዳ አብዱራህማን ባደረጉት ንግግር፤ የክልሉ መንግስት የኢንቨስትመንት አስተዳደርን በማሻሻል የሀገር ውስጥና የውጭ ባለሃብቶችን በስፋት ለማሳተፍ በትኩረት እየሰራ መሆኑን ባደረጉት ክትትል ማረጋገጣቸውን ገልጸዋል።
በክልሉ ያለውን ምቹ መደላድል በመጠቀምም በርካታ የሀገር ውስጥና የውጭ ባለሃብቶች በኢንቨስትመንት ዘርፉ በመሳተፍ ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
በኢንቨስትመንት ዘርፉ የስራ እድል ለመፍጠር፣ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን ለመተካት፣ የወጭ ንግድ ለማሳደግ ብሎም ጥራት ያለውና ተወዳዳሪ ምርቶችን ለማምረት በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።
የክልሉ መንግስት በተለይ ሸገር ከተማ ያላትን መልካ ምድር እና ለባለሃብቶች በተፈጠረው ምቹ ሁኔታ ተጠቅሞ የኢኮኖሚ ማዕከል እንድትሆን ያከናወነው ስራ ውጤታማ መሆኑን ገልጸዋል።
በሸገር ከተማ አዘጋጅነት ዛሬ የተከፈተው አለም አቀፍ የኢንቨስትመንት አውደ ርዕይ ከተማው ለኢንቨስትመንት ያለውን ምቹ ሁኔታ ማስተዋወቅ፣ ልምድ ልውውጥና ለቴክኖሎጂ ሽግግር ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል ብለዋል።
በኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት ማዕረግ የሸገር ከተማ አሰተዳደር ከንቲባ ተሾመ አዱኛ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ሸገርን የኢኮኖሚ ማዕከል የማድረግ ራዕይን እውን ለማድረግ የኢንቨስትመንት ስራን ማስፋፋት ላይ ትኩረት ሰጥተው እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል። እስካሁን በተከናወነው ስራም በርካታ ስኬቶች ተመዝግበዋል ብለዋል።
የተዘጋጀው የሸገር አለም አቀፍ የኢንቨስትመንት አውደ ርዕይ በከተማው ያለውን የኢንቨስትመንት ስራ እንቅስቃሴ እና አካባቢው ለኢንቨስትመንት ያለውን ምቹ ሁኔታ ለማስተዋወቅ እንደሆነ ተናግረዋል።
በአውደ ርዕዩ ላይ በርካታ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ባለሀብቶች ምርትና አገልግሎታቸውን ማቅረባቸውን ያወሱት ከንቲባው፤ ይህም ልምድ ለመለዋወጥ ምቹ መሆኑን ገልጸዋል።
ዝግጅቱ ለቴክኖሎጂ ሽግግር፣ የከተማ ገቢን ለማሳደግና የስራ እድል ለመፍጠር የበኩሉን አስተዋፅኦ እንደሚያበረክትም ጠቁመዋል።
የሀገር ውስጥና የውጭ ባለሃብቶች መዋዕለ ንዋያቸውን በማፍሰስ ሸገር ከተማ ለዘርፉ ልማት ያለውን ምቹ ሁኔታ እንዲጠቀሙ ከንቲባው ጥሪ አቅርበዋል።
የአውደ ርዕዩ ተካፋይ ባለሀብቶችም ፤ በዝግጅቱ በመሳተፋቸው ከሌሎች ባለሀብቶች ጋር የልምድ ልውውጥ ለማድረግ፣ የገበያ ትስስር ለመፍጠርና ምርቶቻቸውን ለማስተዋወቅ እድል እንደፈጠረላቸው ተናግረዋል።