ኮሌጁ ከወዳጅ ሀገራት ጋር ያለውን ወታደራዊ ትብብር እና ዲፕሎማሲ እንዲጠናከር አስተዋጽኦ እያደረገ ነው

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 28/2017 (ኢዜአ)፦የመከላከያ አዛዥነትና ስታፍ ኮሌጅ ከወዳጅ ሀገራት የመጡ ወታደራዊ አመራሮችን በማሰልጠን ወታደራዊ ትብብርና ዲፕሎማሲ እንዲጠናከር አስተዋጽኦ እያደረገ እንደሚገኝ የመከላከያ የትምህርትና ስልጠና ዋና መምሪያ ኃላፊ ሌተናል ጄኔራል ይመር መኮንን ተናገሩ።

የመከላከያ አዛዥነትና ስታፍ ኮሌጅ የ15ኛ ዙር መደበኛ ኮርስ ከፍተኛ መኮንኖችን አስመርቋል። 


 


 

በመርኃ ግብሩ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፣ የመከላከያ የትምህርትና ስልጠና ዋና መምሪያ ኃላፊ ሌተናል ጄኔራል ይመር መኮንን እና የመከላከያ አዛዥነትና ስታፍ ኮሌጅ አዛዥ ብርጋዲየር ጄኔራል ሙሉጌታ አምባቸው፣ ጄኔራል መኮንኖች፣ ወታደራዊ አታሼዎች እና የተመራቂ ቤተሰቦች ተገኝተዋል።

የመከላከያ የትምህርትና ስልጠና ዋና መምሪያ ኃላፊ ሌተናል ጄኔራል ይመር መኮንን በዚሁ ወቅት፤ በኮሌጁ የትምህርትና ስልጠና መርሃ ግብር በተሳካ ሁኔታ ላጠናቀቁ ተመራቂዎች የእንኳን ደስ አላችሁ መልእክት አስተላልፈዋል።

ተመራቂዎቹ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት የተሃድሶ ሂደት ውጤት መሆናቸውን ተናግረው፤ ይህም የመከላከያ ስትራቴጂካዊ አመራር ቁርጠኝነትና ራዕይም ማሳያ እንደሆነ ገልፀዋል።


 

ከወዳጅ ሀገራት የመጡ ወታደራዊ አመራሮችን አሰልጥኖ በማስመረቁ በሀገራት መካከል ለሚኖረው ትብብር እና ወታደራዊ ዲፕሎማሲ ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወትም ተናግረዋል።

የወዳጅ ሀገር ተመራቂዎች በኢትዮጵያ እና በሀገራቸው መካከል ያለውን ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር እንዲሰሩ አደራ ብለዋል።

የመከላከያ አዛዥነትና ስታፍ ኮሌጅ አዛዥ ብርጋዲየር ጄኔራል ሙሉጌታ አምባቸው በበኩላቸው፤ ኮሌጁ የአፍሪካ እህት ሃገራት መኮንኖች ስልጠና መስጠቱን ተናግረዋል።


 

ኮሌጁ ከስልጠናው ባሻገር  ለቀጣናዊ ትብብር ዘላቂ መሠረት የሚሆን ወዳጅነት መገንባት መቻሉን ጄኔራሉ ተናግረዋል።

ከኬንያ የመጣችውና ትምህርቷን ተከታትላ የተመረቀችው ሌተናል ኮሎኔል ሀዋ ሀድጃ አይዛክ የመከላከያ አዛዥነትና ስታፍ ኮሌጅ በአፍሪካ ሀገራት ትብብርና ወዳጅነት የሚያጠናክር ተግባር እያከናወነ ይገኛል ብላለች።


 

በኮሌጁ በነበራት ቆይታ ሙያዋን በተሻለ መልኩ መፈፀም የሚያስችል እውቀት ማግኘቷን ተናግራለች።

ስልጠናው በሀገራት መካከል ያለውን ትብብር ይበልጥ ለማጠናከር የሚያስችል እንደሆነ የተናገረው ከሩዋንዳ የመጣው ሜጀር ጆን ኬነዲ ንዲዛዬ ነው።


 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም