የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት የዲጂታል አሰራር በጥሩ ምሳሌነት የሚጠቀስ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት የዲጂታል አሰራር በጥሩ ምሳሌነት የሚጠቀስ ነው

አዳማ ፤ ሰኔ 28/2017 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት የዲጂታል አሰራር በጥሩ ምሳሌነት የሚጠቀስ መሆኑን የመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር መሰረት መስቀሌ ተናገሩ።
የባለስልጣኑ የስራ ሃላፊዎች የአገልግሎቱን የአዳማ እና አዲስ አበባ የህክምና መሳሪያዎች እንዲሁም መድሀኒቶች አያያዝና አጠቃቀም ያለበትን ሁኔታ ጎብኝተዋል።
ከጉብኝቱ በኋላ ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡት የመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ መሰረት መስቀሌ፤ በዲጂታል ቴክኖሎጂ የተደገፈው የአገልግሎቱ የመድሀኒትና የህክምና መሳሪያዎች አያያዝ፣ አጠቃቀምና አወጋገድ በጥሩ ምሳሌነት የሚወሰድ መሆኑን ገልጸዋል።
የአገልግሎቱን የቅርንጫፍ መጋዘኖችን ከዋና መስሪያ ቤቱ መጋዘን ጋር በዲጂታል ቴክኖሎጂ በማገናኘት ቁጥጥርና አሰራሩን ቀልጣፋ ማድረግ መቻሉንም አድንቀው የመድኃኒት ብልሽት፣ ብክነት፣ ሌብነትና ብልሹ አሰራርን መከላከል የሚያስችል መሆኑን አንስተዋል።
የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈባቸው መድ`ሃኒቶችና የህክምና መገልገያ ቁሳቁሶችም በአግባቡ ተለይተው እየተቀመጡና አስተማማኝ በሆነ መልኩ እየተወገዱ መሆኑን አረጋግጠናል ብለዋል።
የማቀዝቀዣ ማሽኖች በመጋዘኖች አግባብ የሆነ አገልግሎት እየሰጡ መሆኑንም በጉብኝታችን አይተናል ያሉት ዋና ዳይሬክተሯ የሚወገዱ መድኃኒቶችና የህክምና ቁሳቁሶች እንዲሁም ኬሚካሎች የሚወገዱበት የአዳማ ማዕከል ደረጃውን የጠበቀ መሆኑንም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አብዱልቃድር ገልገሎ፤ በአገልግሎቱ 19 ቅርንጫፎች እና 63 መጋዝኖች የዲጂታል አሰራር ተግባራዊ መደረጉን ገልጸዋል።
ከግዥና ስርጭት በተለይም ከተገዙበት አገር ጀምሮ እስከ ክምችት እንዲሁም የስርጭት ሰንሰለቱን በተመለከተ በቀላሉ መከታተልና መቆጣጠር የሚያስችል አሰራር ተግባራዊ መሆኑን አንስተዋል።
በቀጣይም ዓለም አቀፍ የማከማቻ መጋዘኖችን ደረጃ የጠበቀ የማስፋፊያ ስራ የማከናወን እቅድ ተይዞ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።