በመዲናዋ ተገንብተዉ የተጠናቀቁ ከ15 ሺህ 960 በላይ ፕሮጀክቶች ከነገዉ ጀምሮ ለአገልግሎት ክፍት ይሆናሉ

አዲስ አበባ፣ሰኔ 28/2017 (ኢዜአ)፦በመዲናዋ ተገንብተዉ የተጠናቀቁ ከ15 ሺህ 960 በላይ ፕሮጀክቶች ተመርቀዉ ከነገዉ እለት ጀምሮ ለአገልግሎት ክፍት እንደሚሆኑ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ እናትዓለም መለሰ ገለፁ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ እናትዓለም መለሰ፤በ2017 በጀት ዓመት በመዲናዋ የተገነቡ ፕሮጀክቶችን አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

በዚህም ከተማ አስተዳደሩ በ2017 በጀት ዓመት ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታቸው የጎላ ዘርፈ-ብዙ የልማት ስራዎችን በማቀድና ተግባራዊ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡

ለአገልግሎት ክፍት ከሚሆኑት እና ከሚመረቁትፕሮጀክቶች መካከል የመንገድ፣ የውሃ፣ የቤቶች ልማት ፣ የመስሪያ ቦታዎች፣ የወጣቶች ስፖርት ማዘወተሪያ ሜዳዎች፣ በአረንጓረዴ ልማት የተሰሩ እና ሌሎች ለህብረተሰቡ ፋዳቸው ጉልህ የሆኑ ፕሮጀክቶችን ያካተቱ ናቸው ተብሏል፡፡

ፕሮጀክቶቹ በ91 ቢሊዮን ብር ወጪ በመንግስት እና በ4 ቢሊየን ብር ወጪ በህብረተሰቡ ተሳትፎ የተገነቡ ሲሆን፤የተጠቀሰው በጀት ብቻ ሳይሆን ሌሎች በሂደት ላይ ያሉ ፕሮጀክቶችም በፈጣን ክትትል ሥራው ውስጥ እንዳሉ ወ/ሮ እናት ዓለም መለሰ በሰጡት ማብራሪያ ገልፀዋል፡፡

በተጨማሪም የከተማ አስተዳደሩ በበጀት ዓመቱ አጠቃላይ ከተያዘለት በጀት ውስጥ 71 በመቶ የሚሆነዉን ለካፒታል ፕሮጀክት ግንባታ እና ለድህነት ቅነሳ ፕሮግራም እንዲውል በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

እንዲሁም ለትራንስፖርት ለዳቦ ፋብሪካ ድጎማ፣ለባሶች ግዥ፣ለተማሪዎች ምገባ፣ ለጤና መድህን ፕሮግራሞች ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ እንደሚገኝም የቢሮ ኃላፊዋ አስረድተዋል፡፡

የከተማ አስተዳደሩ ለወጣቶች ስራ እድል በሰጠዉ ትኩረት ከ366ሺ በላይ ለሚሆኑ ወጣቶች የስራ ዕድል እንደተፈጠረላቸውም ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም