ወጣቶች ሰላምን ለማጽናት በሚከናወኑ ተግባራት የሚያበረክቱትን አስተዋጽኦ ይበልጥ ማጠናከር ይገባቸዋል

አዲስ አበባ፣ሰኔ 28/2017 (ኢዜአ)፦ወጣቶች ሰላምን ለማጽናት በሚከናወኑ ተግባራት ውስጥ የሚያበረክቱትን አስተዋጽኦ ይበልጥ ማጠናከር እንደሚጠበቅባቸው በብልፅግና ፓርቲ የወጣቶች ክንፍ ገለጸ።

"ሀገሬን እገነባለሁ ሀላፊነቴን እወጣለው" በሚል መሪ ሀሳብ በሀገሪቱ ሲካሄድ በቆየው ውይይት የማጠቃለያ መድረክን አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ተሰጥቷል።


 

በመግለጫው ላይ በብልፅግና ፓርቲ የወጣቶች ክንፍ ምክትል ፕሬዝዳንት እና የጽህፈት ቤት ሀላፊ አባንግ ኩመዳን እንደተናገረችው በሀገር አቀፍ ደረጃ ለአንድ ወር ሲካሄድ በቆየው ውይይት ከ4 ሚሊየን በላይ ወጣቶች ተሳትፈዋል።

በዚህም የበጎ ፍቃድ ስራዎች ፣ የኪነ ጥበብ ዝግጅቶችና የተለያዩ ሑነቶች መካሄዳቸውንም ገልጻለች።

በሀገረ መንግስትና በሰላም እሴት ግንባታ እንዲሁም በሚዲያ አጠቃቀም ላይ ያተኮረ ውይይት  ከታችኛው አደረጃጀት ጀምሮ በመላው አገሪቱ ሲካሄድ መቆየቱንም ተናግራለች።

በነገው እለትም ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት የማጠቃለያ መድረክ እንደሚካሄድ ገልጻ፤ ከመላው አገሪቱ የተውጣጡ ከ1 ሺህ 700 በላይ ወጣቶች እንደሚሳተፉ ጠቅሳለች።

የማጠቃለያ መድረኩ የሰላም አምባሳደርነት ሚናቸውን ይበልጥ እንዲያጠናክሩ አቅም የሚፈጥሩበት መሆኑንም ተናግራለች። 

በብልፅግና ፓርቲ የወጣቶች ክንፍ ምክትል ፕሬዝዳንት ፈዲላ ቢያ በበኩሏ ወጣቶች የዘመኑ አርበኝነት የሆነውን ሰላም የማጽናት ሚናቸውን ሊያጠናክሩ እንደሚገባ ነው የተናገረችው።
 


 

ኢትዮጵያ ለአፍሪካ የብልጽግና ተምሳሌት ለመሆንና ለአለም የብልጽግና አርአያ ለማድረግ የተጀመረውን ራዕይ እውን ለማድረግ ትልቁ መሰረት ሰላም መሆኑንም ጠቅሳለች። 

የማጠቃለያ መደረኩ ተሳታፊ ወጣቶች ለሰላም አርአያ ሆነው ሌሎች በርካታ ወጣቶች ለሰላም ዘብ እንዲሆኑ ማድረግን ያለመ መሆኑንም ገልጻለች ።

በሰላም ሚኒስቴር የብሄራዊ በጎ ፍቃድ አገልግሎት መሪ ስራ አስፈጻሚ ገመቺስ ኢቲቻ በአገሪቱ ለሰላም ግንባታ ወጣቶች  አስተዋጽኦ እያበረከቱ እንደሚገኙ ነው የገለጹት።


 

በአገር አቀፍ ደረጃ በተደረጉት ውይይቶች ልማትንና መልካም አስተዳደርን በመሳሰሉ ጉዳዮች ዙሪያ ወጣቶች ጥያቄዎች በማቅረብ በየደረጃው ሲመለሱላቸው መቆየቱን ጠቅሰዋል።በማጠቃለያ መደረኩም ተጨማሪ ምላሽ እንደሚሰጥ ጠቁመዋል።

ወጣቶች በበጎ አድራጎት ስራዎች፣ የገጠር በጎ ፍቃድ አገልግሎት እንዲሁም በኮሪደር ልማት ስራዎች ላይ እያበረከቱ ያለውን አስተዋጽኦ አጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባም  ተናግረዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም