በእውቀትና በሥነ ምግባር የታነፀ ትውልድን ለመገንባት የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዘርፉ የድርሻውን ሊወጣ ይገባል

ባህር ዳር፣ ሰኔ 28/2017 (ኢዜአ)፦በአማራ ክልል በዕውቀትና በሥነ ምግባር  የታነፀ ትውልድ ለመገንባት በሚደረገው ጥረት የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዘርፉ የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስገነዘበ።

ቢሮው ከሚዲያና ኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች ጋር የትምህርት ሚዲያ ፎረም የምክክር መድረክ ዛሬ አካሂዷል።

በምክትል ርዕሰ መሰተዳድር ማዕረግ የማህበራዊ ክላስተር ዘርፍ አስተባባሪና የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ/ር) በመድረኩ እንደገለጹት፣ ሀገራዊ ብልጽግናን ማረጋገጥ የሚቻለው በዕውቀትና በሥነ ምግባር የታነፀ ትውልድ መገንባት ሲቻል ነው። 


 

ለእዚህም ህፃናትን ከትምህርት ገበታ ውጭ የሚያደርጉ አካላትን ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ በማድረግ ትውልድ የመገንባት ሂደትን ማጠናከር ይገባል ብለዋል።

ሁሉም ባለድርሻ አካላት ለትምህርት ስራ መጠናከር በያገባኛል መንፈስ እንዲንቀሳቀሱ ከሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዘርፉ ብዙ እንደሚጠበቅ ሙሉነሽ (ዶ/ር) አሳስበዋል።

በ2018 የትምህርት ዘመን ያለፉት ሁለት ዓመታትን ማካካስ የሚያስችሉ ሥራዎች እንደሚከናወኑ ጠቁመው፣ በክረምት የቅድመ ዝግጅት ሥራም ህብረተሰቡን በማስተባበር የተጎዱ ትምህርት ቤቶችና የተማሪ ወንበሮችን ጠግኖ ለአገልግሎት ለማብቃት ይሰራል ብለዋል።

የክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን ቢሮ ምክትል ኃላፊ ወይዘሮ ትብለጥ መንገሻ በበኩላቸው እንደገለጹት በትምህርት ዘርፍ የገጠመውን ስብራት ለመጠገን ባለድርሻዎች አስተዋጿቸውን ማጠናከር አለባቸው።

የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዘርፉ ለትምህርት ውጤታማነት እያከናወነ ካለው ሥራ በተጨማሪ ህብረተሰቡ  ልጆቹን ወደ ትምህርት ቤት እንዲልክ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባም አሳስበዋል።


 

በክልሉ ለትምህርት ዘርፍ ስኬት ህዝቡን የማስገንዘብና የማሳወቅ ተግባሩን አጠናክሮ ይቀጥላል ያሉት ደግሞ የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ሙሉቀን ሰጥዬ ናቸው። 

ለዚህም ቀደም ሲል በትምህርት ትልቅ ደረጃ ላይ የደረሱ ሰዎችን በመጋበዝ ልምዳቸውን ለሌሎች እንዲያካፍሉ ኮርፖሬሽኑ በትኩረት ይሰራል ብለዋል።

ተማሪዎች የሚያጋጥማቸውን የትምህርት ቁሳቁስ እጥረት ለማቃለል የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ድጋፍ እንዲያደርጉ ሚዲያው የቅስቀሳና የማስገንዘብ ሚናውን በሃላፊነት ስሜት እንደሚወጣም ተናግረዋል። 

በመድረኩ የሚዲያና ኮሙኒኬሽ ዘርፍ አመራሮችና ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም