ማህበሩ በክልሉ የተጎዱ የህብረተሰብ ክፍሎችን በዘላቂነት ለማቋቋም እያበረከተ ያለውን አስተዋጽኦ አጠናክሮ ይቀጥላል

ዲላ፤ ሰኔ 28/2017 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎች የተጎዱ የህብረተሰብ ክፍሎችን በዘላቂነት ለማቋቋም በሚደረገው ጥረት እያበረከተ ያለውን አስተዋጽኦ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገለጸ።

በክልሉ ጌዴኦ ዞን የማህበሩ 90ኛ ዓመት የምስረታ በዓል በደም ልገሰና በተለያዩ ዝግጅቶች በዲለ ከተማ ተከብሯል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አማካሪና የማህበሩ የቦርድ ሰብሳቢ ተወካይ አቶ ሳሙኤል ቀቀቦ በወቅቱ እንደገለጹት ማህበሩ በክልሉ በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋ ለተጋለጡ ወገኖች ፈጣን ሰብዓዊ ድጋፍ እያደረገ ይገኛል።


 

በክልሉ ጎፋና ሌሎች ዞኖች በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋ ተጎድተው የነበሩ ወገኖችን በዘላቂነት ለማቋቋም 296 መኖሪያ ቤቶችን ግንባታ በተያዘው ዓማት ማከናወኑንም ለአብነት ጠቅሰዋል።

ማህበሩ በክልሉ በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎች የተጎዱ የህብረተሰብ ክፍሎችን በዘላቂነት ለማቋቋም የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።

በክልሉ ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ በመጠንና በዓይነት እየሰፉ መምጣታቸውን ያነሱት አቶ ሳሙኤል፣ ማህበሩን ለማጠናከር የአባላትን ቁጥር ማሳደግና ቋሚ የገቢ ምንጭ መፍጠር ያስፈልጋል ብለዋል።

በዞኑ የማህበሩ አባላትን ቁጥር በማሳደግ ሰብአዊ ድጋፉን ለማጠናከር በትኩረት እንደሚሰራ የተናገሩት ደግሞ የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዝናቡ ወልዴ (ዶ/ር) ናቸው።

በተለይ አባላትን የማፍራቱን ሥራ ከክረምት በጎ ፍቃድ ጋር በማስተሳሰር  ይሰራል ብለዋል።


 

ለዚህም በየደረጃው የሚገኝ መዋቅር ህዝቡን በማስተባበርና የማህበሩ የክብር አባል ጭምር በማድረግ የድርሻውን መወጣት እንዳለበት አስገንዝበዋል።

በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር የጌዴኦ ዞን ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ወንድወሰን ዳካ በበኩላቸው እንዳሉት፣ ማህበሩ በዞኑ ሰብዓዊ ድጋፍ ከማድረግ በተጨማሪ በበጎ ፍቃድ አገልግሎትና በአካባቢ ጥበቃ ሥራ እየተሳተፈ ነው።

እያደገ የመጣውን የሰብአዊ ድጋፍ ፍላጎት ለማጠናከር የአባላት ቁጥርን ማሳደግ እንደሚገባ ጠቅሰው፣ የዞኑ ማህበረሰብ የማህበሩ አባል በመሆን የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።


 

የማህበሩ አባል በመሆን በተለያዩ ሰብአዊ ድጋፎች ላይ እየተሳተፈ መሆኑን የተናገረው ወጣት ትግስቱ አበራ በበኩሉ፣ የማህበሩን 90ኛ ዓመት ምስረታ ምክንያት በማድረግ በተዘጋጀ የደም ልገሳ መርሀግብር ላይ መሳተፉን ተናግሯል።


 

በቀጣይም ማህበሩ በሚያከናውናቸው የሰብአዊ ተግባራትና ማህበራዊ ሃላፊነቱን ለመወጣት በሚያደርገው ጥረት ተሳትፎውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጧል።

በመድረኩ የክልሉ የመንግስት ሥራ ሃላፊዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት መሪዎች እና በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ተሳታፊ ሆነዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም