የአጋሮ ከተማ የኮሪደር ልማት ከተማዋን ለነዋሪዎችና ጎብኚዎች ይበልጥ ምቹ አድርጓል

ጅማ፤ ሰኔ 28/2017 (ኢዜአ) ፡-  የአጋሮ  የኮሪደር ልማት የከተማውን መልካም ገጽታ ከማጉላት ባለፈ  ከተማዋን ለነዋሪዎችና ጎብኚዎች ይበልጥ  ምቹ  በማድረግ ለውጥ ማምጣቱ ተገለጸ። 

የከተማው  የኮሪደር ልማት 12 ነጥብ 4 ኪሎሜትር በመጠናቀቅ ላይ እንደሚገኝ የከተማው አስተዳደር አስታውቋል።  


 

ከአጋሮ ነዋሪዎች መካከል  አቶ ሀፊዝ ከድር በሰጡት አስተያየት፤  የኮሪደር ልማቱ እግረኛና ተሽከርካሪ በተጨናነቀ ሁኔታ የሚጓዝበት  የነበረውን  ሂደት በመቀየር  ይበልጥ  ምቹ  ማድረጉን  ተናግረዋል። 


 

ልማቱ የአጋሮን ከተማ መልካም ገጽታ በማጉላት  ለነዋሪዎችና ጎብኚዎች  ከቀድሞ በተሻለ ምቹ በመሆን  ለውጥ ማምጣቱን ገልጸዋል።

ሌላው የከተማዋ ነዋሪ መምህር ሲሳይ ማረጌ አጋሮ ፤ በኮሪደር ልማቱ መንገድን ከማስፋት ባሻገር  የእግረኛ መንገድ መለየቱና   አካፋይ መተላላፊያ   ላይ የተተከሉት ችግኞች  አረንጓዴን በማልበስ ጭምር  የከተማዋን  ውበት ይበልጥ ጎልቶ እንዲወጣ ማስቻሉን  ተናግረዋል።


 

የኮሪደር ልማቱ ከተማዋን   ለነዋሪዎች ምቹና ማራኪ ከማድረጉ ባለፈ ለበርካታ ሰዎች የስራ እድል  መፍጠሩን የገለጹት ደግሞ  አቶ ነቢል አሊ ናቸው።

የተተከሉ ሳሮች እና የተገነቡ ፋውንቴኖች ለአጋሮ ከተማ ልዩ ውበት  መሆኑንና ልማቱ ተጠናክሮ እንዲቀጥል እንደሚደግፉ ተናግረዋል።


 

የአጋሮ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ነዚፍ መሀመድአሚን በበኩላቸው፤ የከተማው  የኮሪደር ልማት 12 ነጥብ 4 ኪሎ ሜትር በመጠናቀቅ ላይ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።


 

ልማቱ የአረንጓዴ ልማት፣ ፋዎንቴኖችና ኮፊ ኮርነሮች የተካተቱበት ነው ያሉት ከንቲባው ከ10ሺ በላይ ለሚሆኑ ሰዎች የስራ እድል የፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም