ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር 90ኛ ዓመት የምስረታ በዓል ምክንያት በማድረግ የደም ልገሳ ተካሄደ

ጂንካ፤ ሰኔ 28/2017(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር 90ኛ ዓመት የምስረታ በዓል ምክንያት በማድረግ በጂንካ ከተማ የደም ልገሳ መርሃ ግብር ተካሄደ።

ለሰው ልጆች ሁሉ ሰብአዊ አገልግሎት በመስጠት የሰዎችን ህይወት ለማትረፍ፣ ድጋፍና እገዛ ለማድረግ ከመቼውም ጊዜ በላይ ዝግጁ መሆናቸውን የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል አባላት እና ሰራተኞች ተናግረዋል።


 

በመርሃ ግብሩ ላይ ደም ከለገሱት የማህበሩ አባላት መካከል ወጣት እሸቱ ክፍሌ፤ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ አደጋዎች ፈጥኖ የሚደርስ የወገን አለኝታ መሆኑን ተናግሯል።

በመሆኑም የዚህ ማህበር አባል በመሆኑ ክብር እንደሚሰማው ገልፆ ፤ በበጎ ፍቃደኝነት የሚሰጠውን የደም ልገሳ አጠናክሮ መቀጠሉን ተናግሯል።


 

የማህበሩን 90ኛ ዓመት የምስረታ በዓል ከስጦታዎች ሁሉ ውድ የሆነውን ደም በመለገስ በማክበሩም ደስተኛ መሆኑን ገልጿል።

ሌላው የማህበሩ አባል ወጣት ብርሃኑ ኦልጅራ፤ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር የበጎ አድራጎት ፈር ቀዳጅና የበጎነት ተምሳሌት መሆኑን ተናግሯል።


 

የዚህ ማህበር የብዙ ዓመታት አባል በመሆን አገልግሎት በመስጠቱና የምስረታ በዓሉን ሲያከብር ለ17ኛ ጊዜ ደም በመለገሱ መደሰቱን ገልጿል።

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር በትውልድ ቅብብሎሽ የሚዘልቅ ለሰው ልጆች ሁሉ ለበጎነት የሚሰራ በመሆኑ ሁላችንም አጋዥና ደጋፊ እንሁን በማለት ወጣቶቹ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

የጂንካ ደም ባንክ አገልግሎት አስተባባሪ አለሙ አንክሺ፤ የማህበሩን የምስረታ በዓል ምክንያት በማድረግ የማህበሩ ሰራተኞች እና አባላት ደም በመለገስ ላበረከቱት ድጋፍ አመስግነው፤ ይህ የበጎ ፍቃድ ተግባር በቀጣይም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።


 

በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር የደቡብ ኦሞ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ስራ አስኪያጅ አቶ ጥላሁን ቢሻው፤ ማህበሩ በአሪ እና በደቡብ ኦሞ ዞን ለሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች ፈጣን ምላሽ በመስጠት ኃላፊነቱን መወጣቱን አንስተዋል።


 

ከፈጥኖ ደራሽ የበጎ አድራጎት ስራዎች ባሻገር የንፁህ መጠጥ ውሃ ተደራሽ በማድረግ እንዲሁም በሌሎች ማህበረሰብን በሚጠቅሙ የአገልግሎት መስኮች እየተሳተፈ መሆኑን ገልጸዋል።


 

በዛሬው ዕለትም የ90ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን ምክንያት በማድረግ የደም ልገሳ መርሃ ግብር መከናወኑን ተናግረዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም