ቀጥታ፡

የኢትዮጵያን የኮንፈረንስ ቱሪዝም ተመራጭነት የበለጠ ማሳደግ ይገባል-የምክር ቤት አባላት

አዲስ አበባ፣ሰኔ 28/2017 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያን የኮንፈረንስ ቱሪዝም ተመራጭነት የበለጠ ማሳደግ እንደሚገባ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የመንግስትን የ2017 በጀት ዓመት የዕቅድ አፈፃጸም አስመልክቶ ከትናንት በስተያ ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ መስጠታቸው ይታወሳል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት፤ በኢትዮጵያ በተያዘው ዓመት ብቻ ከ150 በላይ ዓለም አቀፍ ኮንፍረንሶች ተካሂደዋል። 

ይህም ከባለፈው አመት ጋር ሲነጻጻር በእጥፍ የጨመረ መሆኑን በመጥቀስ።

የዓለም ተቋማት ኢትዮጵያን መርጠው ከመጡባቸው ምክንያቶች መካከልም በኢሚግሬሽን ላይ የተደረገው ሪፎርም፣ በአየር መንገድ አገልግሎት ፣የቱሪስት መዳረሻዎችና የኮሪደር ልማትን ለአብነት አንስተዋል።

በበጀት ዓመቱ 1 ነጥብ 3 ሚሊየን የውጭ ቱሪስቶች ኢትዮጵያን መጎብኘታቸውንና  ይህም እስካሁን ካለው ከፍተኛ ቁጥር መሆኑን ነው ያነሱት።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላትም በዚህ ጉዳይ ይስማማሉ።

የምክር ቤቱ አባል ዑስታዝ ካሚል ሸምሱ እንደሚሉት፤ የኢትዮጵያ ፈጣን ልማትና አንጻራዊ ሰላም እንዲሁም በአለምአቀፍ ደረጃ ያላት ተቀባይነት መጨመር ለኮንፈረንስ ቱሪዝም ዘርፉ መነቃቃት ምክንያት ሆኗል።


 

ከተማዋ የአፍሪካ መዲናና የአለምአቀፍ ተቋማት መቀመጫ መሆኗም ለኮንፈረንስ ተመራጭ አድርጓታል ነው ያሉት።

ሌላው የምክር ቤት አባል ከፈና ኢፋ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ለኮንፈረንስ ምቹ መሰረተ ልማቶችን ለማሟላት ያደረገችው ጥረትና እየታየ ያለው ሰላም በአህጉራዊና ዓለምአቀፍ ስብሰባዎችን እንድታስተናግድ ዕድል ፈጥሯል።

በኢትዮጵያ እየታየ ያለውን ሰላም ወደ ዘላቂ ሰላም በመቀየር የአገሪቷን ዓለምአቀፍ ተቀባይነትና ተሰሚነት የሚያጎሉ ሥራዎችን መስራት እንደሚገባም አባላቱ ተናግረዋል።


 

ከዚህ አኳያ የምክር ቤት አባላቱ ሰላምን የሚያጸኑና የህዝቡን አብሮነት የሚያጎለብቱ ጉዳዮች ላይ በትኩረት እንደሚሰሩ ነው የተናገሩት።

በተያዘው ዓመት የአንድነት ፓርክ፣ ሳይንስ ሙዚየም፣ የወዳጅነት ፓርክና ቤተ መንግስትን 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሰዎች የጎበኙ ሲሆን፤ በዚህም ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መገኘቱንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አብራርተዋል።።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም