መንግስት ለሰላም ያለው የማይናወጥ አቋም የሚደነቅ ነው - ኢዜአ አማርኛ
መንግስት ለሰላም ያለው የማይናወጥ አቋም የሚደነቅ ነው

አዲስ አበባ፣ሰኔ 28/2017 (ኢዜአ)፦መንግስት ለሰላም ያለው የማይናወጥ አቋም የሚደነቅ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 42ኛ መደበኛ ስብሰባውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት አካሄዷል፡፡
በዚሁ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በማብራሪያቸው ከዚህ በፊት በኢትዮጵያ ውስጥ ተከስተው የነበሩ ግጭቶች ተፈትተው አሁን ላይ አንጻራዊ ሰላም ሰፍኗል ብለዋል።
መንግስት በአንዳንድ የአገሪቱ አካባቢዎች በተሳሳተ ስሌት ነፍጥ አንግበው ከሚንቀሳቀሱ ሃይሎች ጋር ለመነጋገር አሁንም በሩ ክፍት መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡
ማብራሪያውን በተመለከተ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች አስተያየታቸውን ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ሰጥተዋል፡፡
አስተያየታቸውን ከሰጡት መካከል መምበረ አግዘው እንዳሉት መንግስት ሰላምን ከማረጋገጥ ጎን ለጎን የልማት ተግባራትን በማከናወን የዜጎችን ተጠቃሚነት እያረጋገጠ ይገኛል ብለዋል፡፡
በዚህም በአገሪቱ ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ ያለው የማይናወጥ አቋም የሚደነቅ መሆኑን ጠቅሰው፤ በተሳሳተ መንገድ ወደ ሰላም ያልመጡ ራሳቸውን ለውይይት ዝግጁ ማድረግ እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡
ሌላኛው አስተያየት ሰጪ አቶ አለማየሁ ታዬ እንዳሉት ግጭት ያለንበትን ዘመን የማይመጥን፣ ዘርፈ ብዙ ጉዳት የሚያስከትል እንጂ ዘላቂ ሰላምና ልማትን የሚያረጋግጥ አይደለም ብለዋል፡፡
በመሆኑም በተሳሳተ ስሌት ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ አካላት የመንግስትን የሰላም ጥሪ ተቀብለው ለምክክር መዘጋጀት እንዳለባቸው ሃሳባቸውን ሰጥተዋል፡፡
በአንዳንድ አካባቢዎች የሚስተዋሉ ግጭቶች በዘለቂነት ቢቋጩ የነዋሪውን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ መሆኑን አዲስ አበባ ምስክር ናት ያሉት አስተያየት ሰጪ ደግሞ ወይዘሮ ብርቄ ገብረ ዮሐንስ ናቸው፡፡
በመሆኑም ሁሉም ዜጋ ለሰላም በጋራ መስራት እንዳለበት ነው ያነሱት፡፡