ወደ ፖርቶ የተጀመረው በረራ የፖርቹጋል እና ኢትዮጵያን ግንኙነት የበለጠ የሚያጠናክር ነው

 

አዲስ አበባ፣ሰኔ 28/2017 (ኢዜአ)፦ወደ ፖርቶ የተጀመረው በረራ የፖርቹጋልና ኢትዮጵያን ግንኙነት የሚያጠናክርና ለአገራቱ የቱሪዝም እድገት አስተዋፅኦ የሚያበረክት መሆኑን በኢትዮጵያ የፖርቹጋል አምባሳደር ልዊሳ ፋራጎሶ ገለፁ።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሣምንት አራት ጊዜ ወደ ፖርቹጋል ፖርቶ ከተማ አዲስ በረራ መጀመሩ ይታወሳል።


 

በረራው ሁለቱ አገራትን በቱሪዝም፤ንግድና ኢንቨስትመንት በማስተሳሰር ወዳጅነትታቸውን እንዲያጠናክሩ ትልቅ ሚና እንዳለው ታምኖበታል።

አየር መንገዱ ወደ ፖርቶ የጀመረውን በረራን አስመልክቶም ትናንት ምሽት በፖርቶ ከተማ የእንኳን ደህና መጣችሁ መርሃ ግብር ተከናውኗል።

በዚህ ወቅት በኢትዮጵያ የፖርቹጋል አምባሳደር ልዊሳ ፋራጎሶ በኢትዮጵያ በርካታ የልማት የትብብር እድሎች እንዳሉ ተናግረዋል።

በትራንስፖርት አለመተሳሰር ይህን እድል በመጠቀም ረገድ ውስንነት ፈጥሮ መቆየቱን አንስተው፤ አየር መንገዱ ወደ ፖርቹጋል የጀመረው በረራም ችግሩን ለማቃለል ዓይነተኛ ሚና እንዳለው አብራርተዋል።

የፖርቶ ከተማ ቱሪዝም ቦርድ ፕሬዝዳንት ፔድሮ ማርቲንስ በበኩላቸው፣ የአየር መንገዱ ወደፖርቶ በረራ መጀመር የሁለቱን አገራት የቱሪዝም መዳረሻዎች ለማስተዋወቅ አስተዋፅኦ እንዳለው ተናግረዋል።

በፖርቹጋልና ኢትዮጵያ በርካታ የቱሪዝም ስፍራዎች እንዳሉ አንስተው፤ አየር መንገዱ የጀመረው በረራም እነዚህን ስፍራዎች ወደ ልማት ለመቀየር ትልቅ አቅም መሆኑን አብራርተዋል።


 

ፖርቹጋላዊያን ቱሪስቶች የኢትዮጵያ አየር መንገድ በፈጠረው እድል ኢትዮጵያን እንዲጎበኙም ጥሪ አቅርበዋል።

በኢትዮጵያ አየር መንገድ የኢትዮጵያ ሆሊደይና ዲጂታል ዘርፍ ምክትል ፕሬዝዳንት ሃይለመለኮት ማሞ በበኩላቸው፤ ወደፖርቶ የተጀመረው በረራ አየር መንገዱ ከአውሮፓ ጋር ያለው ጠንካራ የትራንስፖርት ትስስር ማሳያ መሆኑን ተናግረዋል።


 

አፍሪካን ከተቀረው ዓለም ጋር ለማስተሳሰር እያከናወናቸው ያሉ ስራዎች አካል ስለመሆኑም አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም