የዲያጎ ጆታ እና ወንድሙ አንድሬ ሲልቫ የቀብር ስነ ስርዓት ተፈጸመ 

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 28/2017(ኢዜአ)፦ ፓርቹጋላውያኑ የእግር ኳስ ተጫዋች ዲያጎ ጆታ እና የወንድሙ አንድሬ ሲልቫ የቀብር ስነ ስርዓት በሰሜናዊ ፓርቹጋል በምትገኘው የትውልድ ስፍራቸው ጎንዶማር ዛሬ ተፈጽሟል። 


 

በቀብር ስነ ስርዓቱ ላይ የሊቨርፑል አሰልጣኝ አርን ስሎት፣ የቡድኑ አምበል ቨርጂል ቫን ዳይክ፣ አንድሪው ሮበርትሰን እና በርካታ የሊቨርፑል ተጫዋቾች፣ የፓርቹጋል አሰልጣኝ ሮቤርቶ ማርቲኔዝ እንዲሁም የብሄራዊ ቡድን አጋሮቹ ብሩኖ ፈርናንዴዝ፣ በርናርዶ ሲልቫ፣ ሩበን ኔቬስ፣ ሩበን ዲያዝ እና ጆአ ካንሴሎ እንዲሁም የቀድሞ የቡድን አጋሮቹ፣ የተለያዩ ክለቦች አመራሮች እና ቤተሰቦቹ ተገኝተዋል።


 

ትናንት በፊፋ ክለቦች የዓለም ዋንጫ በፍሉሜኔንሴ 2 ለ 1 የተሸነፈው የአል ሂላል ቡድን ስብስብ ውስጥ የነበሩት የቅርብ ጓደኛው ሩበን ኔቬስ እና ጆአ ካንሴሎ ከአሜሪካ ወደ ፓርቹጋል በመብረር ስርዓተ ቀብሩ ላይ ታድመዋል። 

ከቀብሩ ስነ ስርዓት ጎንዶማር በሚገኘው ማዘር ቤተ ክርስቲያን የአስክሬን ሽኝት ተደርጓል፡፡


 

ዲያጎ ጆታ እና ወንድሙ አንድሬ ሲልቫ ከትናንት በስቲያ ማለዳ ላይ በማድሪድ ግዛት በሰሜናዊ ፖርቹጋል ወደ ምትገኘው ጋላሲያ ከተማ እያቀኑ ባሉበት ወቅት በሰሜን ምዕራብ ስፔን በምትገኘው ዛሞራ ከተማ በደረሰው ድንገተኛ አደጋ ህይወታቸው አልፏል።

ተጫዋቾቹ ሲጓዙበት የነበረው ላምቦርጊኒ መኪና ሌላ አልፎ ለመሄድ በሚሞክርበት ጊዜ የጎማ መፈንዳት አጋጥሞ መንገድ ስቶ የወጣው መኪና በእሳት በመያያዙ አደጋው ደርሷል። 

የሊቨርፑሉ ዲያጎ ጆታ በ28 ዓመቱ እና በፓርቹጋል ሁለተኛ ዲቪዚዮን ፔናሲፌል ቡድን ሲጫወት የነበረው አንድሬ ሲልቫ በ25 ዓመቱ ህይወታቸው አልፏል።

ዲያጎ ጆታ ከአደጋው መከሰት ቀናት በፊት ከረጅም ጊዜ አጋሩ ሩት ካርዶሶ ጋር ጋብቻ መፈጸሙ የሚታወስ ነው።


 

በተጨማሪም በቅርቡ ከፓርቹጋል ጋር የዩኤፋ ኔሽንስ ሊግ እና ከሁለት ወር ገደማ በፊት ከሊቨርፑል ጋር የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ዋንጫን አንስቷል። 

ሊቨርፑል የዲያጎ ጆታን 20 ቁጥር ማልያ በክብር የሰቀለ ሲሆን የጆታን የሁለት ዓመት ኮንትራት ደሞዝ ለቤተሰቡ እንደሚከፍል አስታውቋል። ቡድኑ የቅድመ ውድድር ዝግጅት መጀመሪያ ጊዜውንም አራዝሟል።  

የዲያጎ ጆታ እና የወንድሙ አንድሬ ሲልቫ ሞት በዓለም እግር ኳስ ውስጥ ትልቅ ድንጋጤን የፈጠረ ሲሆን ፖርቹጋልን ጥልቅ ሀዘን ውስጥ ከቷል።  


 

ያሏቸውን ሁለት ልጆች ያጡት እናት እና አባቱ እንዲሁም ባሏን ያጣቸው ሩት ካርዶሶ ሁኔታ እጅጉን አሳዛኝ ሆኗል። 

የዓለም እግር ኳስ ማህበረሰብ ለወንድማማቾቹ ቤተሰቦች እና ወዳጆች ሀዘኑን በመግለጽ ላይ ይገኛል። 

ዲያጎ ጆታ የሶስት ልጆች አባት ነበር።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም