የሰባተኛውን ጠቅላላ ምርጫ ተደራሽነት ለማስፋት በቴክኖሎጂ የታገዘ ሥራ እየተከናወነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የሰባተኛውን ጠቅላላ ምርጫ ተደራሽነት ለማስፋት በቴክኖሎጂ የታገዘ ሥራ እየተከናወነ ነው

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 28/2017(ኢዜአ)፦ሰባተኛውን ዙር ጠቅላላ ምርጫ ግልፅነትና ተደራሽነት ለማስፋት በቴክኖሎጂ የታገዘ ሥራ እያከናወነ መሆኑን የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ።
ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተጠሪ የሆኑ የዴሞክራሲ ተቋማት የሪፎርም ስራቸውን አስመልክቶ የጋራ የውይይት መድረክ እያካሄዱ ነው።
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሜላተወርቅ ኃይሉ የተቋማቸውን የሪፎርም ስራዎች አስመልክቶ ሪፖርት አቅርበዋል።
በዚሁ ጊዜ ቦርዱ በህዝብና በመንግስት የተጣለበትን ኃላፊነት በአግባቡ ለመወጣት የነበሩበትን የአሰራር ክፍተቶች ለይቶ ለመፍትሄው ሲሰራ መቆየቱን አስታውሰዋል።
በዚህም በህግና በአሰራር፣ በሰው ሃይልና አደረጃጀት ያሉ ክፍተቶች እንዲስተካከሉ ሪፎርም ማድረጉንም አመልክተዋል።
ካለፉት ምርጫ ሂደቶች የተሻሉ ተሞክሮዎችን በመውሰድና ችግሮችን በመለየት ለቀጣዩ ምርጫ የበለጠ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም ነው ያብራሩት።
የሰባተኛውን ዙር ምርጫ ነፃ፣ ገለልተኛና ተዓማኒነት ያለው እንዲሆን በቴክኖሎጂ የታገዘ አሰራር ለመተግበር ዝግጅት እያደረገን ነው ብለዋል።
በዚህም የምርጫ ሂደቱን ፈጣንና ተደራሽ ማድረግ የሚያስችሉ የሞባይል መተግበሪያ በማበልፀግ የዕጩዎችንና የመራጮችን ምዝገባ በቴክኖሎጂ ለማከናወን ስራዎች ተጀምረዋል ነው ያሉት።
ተቋሙ ነፃና ገለልተኛ ሆኖ የተጣለበትን ኃላፊነት ለመወጣት በሰው ሃይልና በአደረጃጀት ራሱን ማብቃት የሚያስችሉ ሥራዎችን እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።
የዕጩዎችና የመራጮችን ምዝገባ ለማካሄድ የሚያግዘው ቴክኖሎጂ አስተማማኝና በቦርዱ ባለሙያዎች የበለፀገ ሲስተም መሆኑንም ገልጸዋል።
ምዝገባው በሞባይል መተግበሪያ፣ በቦርዱ ባለሙያዎች እገዛ እንዲሁም በማኑዋል መንገድ እንደሚከናወንም አመልክተዋል።
የፖለቲካ ፓርቲዎችና መራጮች ስለ ቴክኖሎጂው አጠቃቀም በቂ ግንዛቤ እንዲኖራቸው እገዛ ይደረግላቸዋል ብለዋል።
ለዚህ አሰራር የሚሆን አዋጅ ለምክር ቤቱ መቅረቡንም ነው ያመለከቱት።
የኢትዮጵያ ህዝብ ዕንባ ጠባቂ ዋና ዕምባ ጠባቂ ስመኝ ውቤ በበኩላቸው፤ ተቋሙ የተጣለበትን ኃላፊነት መወጣት የሚያስችለውን ሪፎርም ሲያከናውን ነበር ብለዋል።
በዚህም አስተዳደራዊ በደሎችን መፍታት የሚያስችሉ የሰው ሃይልና አደረጃጀት መፍጠሩን በማንሳት።
በተያዘው በጀት ዓመት 11ወራት ከ2ሺ በላይ አቤቱታዎችን መርምሮ የውሳኔ ሀሳብ መስጠቱን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ፤ የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ላይ የሚደርሱ ጥሰቶችን ማረም የሚያስችሉ ጠንካራ የአሰራር ሥርዓት ተዘርግቶ ወደ ስራ መግባቱን ተናግረዋል።
በተለይም የሰብዓዊ መብቶች ተጥሰዋል የሚሉ አቤቱታዎች ሲቀርቡ በሁለቱም ወገን ያለውን እውነታ በማጣራት ፍትሃዊና ትክክለኛ ሪፖርት እንዲወጣና ጥሰቱ እንዲታረም እየሰራ ነው ብለዋል።
ኮሚሽኑ በዲጂታል ቴክኖሎጂ የታገዘ አሰራር መተግበሩንም ጠቅሰው፤ የሰብዓዊ መብት አያያዝና አጠባበቅ የበለጠ እንዲጠናከር የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።