መከላከያ ሠራዊት በሁሉም ዘርፍ የተደራጀና ዘመናዊ መሳሪያ የታጠቀ በአስተሳሰብና ሥነ-ልቦና የተገነባ ነው - ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ - ኢዜአ አማርኛ
መከላከያ ሠራዊት በሁሉም ዘርፍ የተደራጀና ዘመናዊ መሳሪያ የታጠቀ በአስተሳሰብና ሥነ-ልቦና የተገነባ ነው - ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 28/2017(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በሁሉም ዘርፍ በወጉ የተደራጀ፣ ዘመኑን የዋጀ ዘመናዊ መሳሪያ የታጠቀ በአስተሳሰብና ሥነ-ልቦና የተገነባ ነው ሲሉ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ገለጹ።
የመከላከያ አዛዥነትና ስታፍ ኮሌጅ የ15ኛ ዙር መደበኛ ኮርስ ከፍተኛ መኮንኖችን አስመርቋል።
በመርኃ ግብሩ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፣ የመከላከያ የትምህርትና ስልጠና ዋና መምሪያ ኃላፊ ሌተናል ጀነራል ይመር መኮንን እና የመከላከያ አዛዥነትና ስታፍ ኮሌጅ አዛዥ ብርጋዲየር ጄኔራል ሙሉጌታ አምባቸው፣ ጄኔራል መኮንኖች፣ ወታደራዊ አታሼዎች እና የተመራቂ ቤተሰቦች ተገኝተዋል።
የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ኮሌጁ ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ በሁሉም የመከላከያ ሠራዊት ክፍሎችና ኃይሎች ውስጥ በብቃት የመምራት ችሎታ ያላቸውን ከፍተኛ ታክቲካል የጦር ክፍሎችን፣ የኦፕሬሽናል ውጊያ ሳይንስና ጥበብ ሥልጠና የወሰዱ በርካታ ከፍተኛ መኮንኖች ማፍራቱን ተናግረዋል።
በዚህ ዓመትም በኮሌጁ ስልጠና በመውሰድ በብቃት አጠናቀው ለምረቃ የበቁ ከፍተኛ መኮንኖች የመከላከያ ሠራዊት እያስመዘገበ ያለውን ብቁ የሰለጠነ ፕሮፌሽናል ሠራዊት የመገንባት ጥረት ውጤት መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
አገራዊ እና ተቋማዊ ሪፎርም ከተበሰረበት ጊዜ ጀምሮም ኢትዮጵያ በሁሉም መስክ ከፍተኛ ስኬት እያስመዘገበች እንደምትገኝ ተናግረዋል።
በመከላከያ ተቋማዊ ግንባታ መስክ ከፍተኛ ለውጥ እያስመዘገበች መሆኑን ገልጸው፤ ውጤቱ በቁርጠኛ የመንግስት አመራርና ፅናትን በተላበሱ የሠራዊት አዛዦችና በጀግናው ሠራዊታችን መስዋዕትነት ነው ብለዋል።
የመከላከያ ሠራዊቱን ፕሮፌሽናል በማድረግና በማዘመን በቀጣይ ሊከሰቱ የሚችሉ ስጋቶችን ከሩቅ የማስቀረት እንዲሁም ብሔራዊ አደጋ ቢከሰት በአስተማማኝ መቀልበስ የሚችል አቅም ያለው ሠራዊት ገንብተናል ብለዋል፡፡
በአሁኑ ወቅትም የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በሁሉም ዘርፍ ተለውጦ በወጉ የተደራጀ፣ ዘመኑን የዋጀ ዘመናዊ መሳሪያ የታጠቀ በአስተሳሰብና ሥነ-ልቦና የተገነባ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በተጨማሪም የወታደራዊ ስትራቴጂ ኦፕሬሽን፣ ስልታዊ ጥበብና እውቀትን የተላበሰና ኢትዮጵያን የሚመጥን የአገር መከላከያ ለመገንባት የተቀመጠውን ስትራቴጂ ለማሳካት በትኩረት እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል።
ተመራቂ ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖችም በመከላከያ አዛዥና ስታፍ ኮሌጅ በነበራቸው ቆይታ ያገኙትን ትምህርት፣ የተሟላ እውቀት፤ ክህሎትና አስተሳሰብ በመጠቀም ለዚህ አቅም መሆን አለባቸው ብለዋል።
ተመራቂዎች በሚሰማሩባቸው የሠራዊቱ ክፍሎች የወታደራዊ ሥነ-ምግባር፣ የግዳጅ አፈፃፀም ብቃትና የማይናወጥ ሥነ-ልቦና ተምሳሌትና አርዓያ በመሆን እንዲያገለግሉ አስገንዝበዋል።
ኮሌጁ የኢትዮጵያን መከላከያ ከፍተኛ መኮንኖች ከማብቃት ባሻገር ከወዳጅ አገራት የመጡ ከፍተኛ መኮንኖችን ተቀብሎ በማስተማርና በማሰልጠን ወታደራዊ ትብብርና ዲፕሎማሲ ይበልጥ እንዲጠናከር በማድረግ ላይ መሆኑንም ተናግረዋል ፡፡
በዛሬው ዕለትም ከበርካታ ወዳጅ አገሮች የመጡ ከፍተኛ መኮንኖች በኮሌጁ ሲሰጥ የቆየውን ትምህርት አጠናቀው ለምረቃ መብቃታቸውን አንስተዋል።
ተመራቂ የወዳጅ አገሮች ከፍተኛ መኮንኖች በነበራችው ቆይታ ያገኙትን አቅምና ዕውቀት ለአገራቸው ተልዕኮ እንዲጠቀሙበት ያስገነዘቡት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ፤ ስልጠና የሰጠቻቸውን ኢትዮጵያ ከአገራቸው ጋር ለጠበቀ ወዳጅነት መስራት እንዳለባቸው ተናግረዋል።
ይህ የትምህርትና ስልጠና ትብብርም በአገሮች መካከል ሊኖር የሚችልን ወታደራዊ ዲፕሎማሲ ወደ ከፍተኛ ደረጃ የሚያሸጋግር መሆኑን ጠቅሰው ይህንንም አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል።