የኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ የመደራደር አቅም እየጎለበተ መጥቷል - የምክር ቤት አባላት - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ የመደራደር አቅም እየጎለበተ መጥቷል - የምክር ቤት አባላት

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 28/2017(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ የመደራደር አቅም በተጨባጭ አየጎለበተ መምጣቱን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የ2017 በጀት ዓመት የመንግስትን የሥራ አፈጻጸምን አስመልክቶ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ መስጠታቸው ይታወሳል።
በዚሁ ወቅት ባለፉት ሰባት ዓመታት አገሪቷ ምንም ዓይነት ኮሜርሺያል (ከፍተኛ ወለድ ያለው) ብድር አለመውሰዷን ነው የገለጹት።
ይሁን እንጂ ባለፉት መንግስታት የተከማቸ የውጭ ዕዳ ለመክፈል ከፍተኛ ጥረት ስታደርግና የብድር መክፈያ ጊዜውን ለማራዘም ስትደራደር መቆየቷን አብራርተዋል።
በዚህም ባለፉት አራት ዓመታት ከተለያዩ መንግስታት ጋር በተደረገ ድርድር የ3 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ዕዳ ሽግሽግ መደረጉንም ነው ያነሱት።
አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የ3 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር የዕዳ ሽግሽግ ትልቅ የዲፕሎማሲ ድል ነው ብለዋል።
ብድር ለታለመለት ዓላማ ካልዋለ ለትውልድ ዕዳ መሆኑ እንደማይቀር ጠቁመው፤ መንግስት ይህን ዕዳ ለማቃለል እየወሰዳቸው ያሉ እርምጃዎችንም አድንቀዋል።
ረዳት ፕሮፌሰር ገነነ ገደቦ መንግስት ከተለያዩ አገራት የሚወስዳቸው ብድሮች ለታለመላቸው ዓላማ ማዋልና ብድሩን በጊዜ መመለስ ይገባል ይላሉ።
በከፍተኛ ወለድ የመጡ ብድሮች አገርና ትውልድ ላይ ጫና የሚፈጥሩና ተጨማሪ ልማት እንዳይኖር የሚያደርጉ በመሆኑ መንግስት በድርድር ዕዳውን ማሸጋሸጉ ተገቢ መሆኑንም አንስተዋል።
ሌላዋ የምክር ቤት አባል ነጃት ግርማ (ዶ/ር)፤ ቀደም ሲል አገሪቷን ሲመሩ የነበሩ መንግስታት ለትውልዱ ከፍተኛ ዕዳ አሸጋግረዋል ነው ያሉት።
ከለውጡ ዓመታት በኋላ መንግስት ይህን የትውልድ ዕዳ ለማቃለል እየወሰዳቸው ያሉ እርምጃዎችንም አድንቀዋል።
የተለያዩ መንግስታት የኢትዮጵያን ዕዳ ለማሸጋሸግ ያሳዩት ፍላጎትም አገሪቷ በራሷ ለመልማት ያላትን አቋም ከማየት የመነጨ መሆኑን በማንሳት።
ሌላው የምክር ቤት አባል ፈትህ መህዲ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ባለፉት ስድስት ዓመታት ምንም ዓይነት ከፍተኛ ወለድ ያለው ኮሜርሺያል ብድር አለመውሰዷ ዕዳዋን የመቀነስ ፍላጎቷን ያሳያል።
እንደ እርሳቸው ገለጻ፤ አገሪቷ ቀደም ሲል የወሰደቻቸው ብድሮች የእፎይታ ጊዜ ለማግኘት የተደረገው ሽግሽግ የአገሪቷን የመደራደር አቅም መጎልበት ያሳያል።
የምክር ቤቱ አባል ሰሚራ የሱፍም በዚህ ሀሳብ ይስማማሉ።
የዕዳ ሽግሽጉም በዓለም አቀፍ ደረጃ ኢትዮጵያ ያላትን የዲፕሎማሲ ግንኙነት መጠናከር የሚያሳይ ነው ብለዋል።
ምክር ቤቱ የሚቀርቡለት የብድር ስምምነቶች ለታለመላቸው ዓላማ እንዲውሉ በአግባቡ በመፈተሽ እንደሚያጸድቅም ነው አባላቱ የገለጹት።