የአረንጓዴ አሻራ ልማትን ዘርፈ ብዙ ጥቅም በተግባር የተገነዘብን በመሆኑ ችግኞችን ለመትከል እና ለመንከባከብ ተዘጋጅተናል

አሶሳ፤ ሰኔ 28/2017 (ኢዜአ)፦ የአረንጓዴ አሻራ ልማትን ዘርፈ ብዙ ጥቅም በተግባር የተገነዘብን በመሆኑ ችግኞችን ለመትከል እና ለመንከባከብ ተዘጋጅተናል ሲሉ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የአረንጓዴ አሻራ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ላይ የተሳተፉ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተናገሩ።

የ2017 የአረንጓዴ አሻራ ማስጀመሪያ መርሃ-ግብር በክልሉ በኡራ ወረዳ ሰልጋ 20 ንዑስ ተፋሰስ ልማት ላይ ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን በተገኙበት በይፋ ተጀምሯል።

በመርሃ ግብሩ ላይ ከተገኙት መካከል ኢዜአ ያነጋገራቸው የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የአረንጓዴ አሻራ ልማትን ዘርፈ ብዙ ጥቅም በተግባር የተገነዘብን በመሆኑ ችግኞችን ለመትከል እና ለመንከባከብ ተዘጋጅተናል ብለዋል።

ካነጋገርናቸው መካከል አቶ  አብዱላሂ ሙሀመድ እና ወይዘሮ ሺዋጋ አለሙ፤ የአረንጓዴ አሻራ ውጤት ምግብም፣ ጥላና ከለላም እየሆነ እኛንም ተፈጥሮንም እየጠበቀ ይገኛል ሲሉ ተናግረዋል።

በአካባቢያቸው መሬት እንዲያገግም እና ለእንስሳት መኖ በቅርበት እንዲያገኙ እያደረገም ስለመሆኑ አንስተዋል።

በተለይም በተፋሰስ ልማት ላይ የሚተከሉ ችግኞች የመጽደቅ መጠናቸው ከፍተኛ በመሆኑ የተፋሰስ ልማት እና የችግኝ ተከላን በተጠናከረ መልኩ የሚያስቀጥሉ መሆኑን አረጋግጠዋል።


 


 

ሌላው በመርሃ ግብሩ ላይ የተሳተፉት መቶ አለቃ በሱፍቃድ ገላን፤ የመከላከያ ሰራዊት የሀገርን ዳር ድንበር ከማስጠበቅ ባለፈ በተለያዩ የልማት ስራዎች ላይ የነቃ ትብብርና ተሳትፎ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም መሰረት የልማት አጋር በመሆን በዛሬው እለት በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሻራቸውን ማኖራቸውን ገልጸዋል።


 

በዚሁ መርሃ ግብር ላይ የተሳተፈችው ተማሪ ፎዚያ ሙሀመድ፤ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ለትውልድ የሚተርፍ አሻራ በመሆኑ የዚሁ ታሪክ አካል ለመሆን ተገኝቻለሁ ብላለች።

በመርሃ ግብሩ ላይ የክልሉ ርእሰ መስተዳደር አሻድሊ ሀሰንን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ አመራሮች፣ የፀጥታ አካላት እና የአካባቢው ማህበረሰብ ክፍሎች ተገኝተው አሻራቸውን አኑረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም