የስፖርቱን ዘርፍ ይበልጥ ለማሳደግ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የስፖርቱን ዘርፍ ይበልጥ ለማሳደግ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው

ባሕርዳር ፤ ሰኔ 28/2017(ኢዜአ)፡-ምቹ የስፖርት ሜዳዎችን ከመገንባት ጀምሮ የስፖርቱን ዘርፍ ይበልጥ ለማሳደግ የሚያስችሉ ተግባራት በትኩረት እየተከናወኑ መሆኑ ተገለጸ።
የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የሚያዘጋጀው ስለ ኢትዮጵያ ምዕራፍ ሁለት 7ኛ የፓናል ውይይት መድረክ "ስፖርት ለአሸናፊ ሀገር " በሚል መሪ ሀሳብ በባሕር ዳር አለም አቀፍ ስታዲየም እየተካሄደ ነው።
በመድረኩ የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ፣ የስፖርት ባለሙያዎች፣አሰልጣኞችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።
የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ የፓናል ውይይቱ ሰጀመር ባደረጉት ንግግር እንዳሉት፤ ስፖርት ብቁና ንቁ ዜጋ ለመፍጠር የሚያግዝ የውድድር መድረክ ነው።
ስፖርት ህብረ ብሔራዊት ኢትዮጵያን ለመገንባት ከንግግር ባለፈ በተግባር የሚገልጽና ሀገራዊ ስሜት የሚንፀባረቅበት ሰላማዊ ውድድር መሆኑን ገልጸዋል።
በስፖርት ልማት ላይ መዋዕለ ንዋይ ማፍሰስ ከማህበራዊ ዘርፉ በላይ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳውም የጎላ በመሆኑ የግል ባለሀብት ጨምሮ ሁሉም አካል በዘርፉ ልማት ላይ ሊሳተፉ እንደሚገባ አመልክተዋል።
የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ተስፋሁን ጎበዛይ በበኩላቸው፤ መንግስት የስፖርት ዘርፉን ሁለንተናዊ ፋይዳ በመረዳት ትኩረት ሰጥቶ እየደገፈ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ምቹ የስፖርት ሜዳዎችን ከመገንባት ጀምሮ ለስፖርት ዘርፉ ዕድገት አስቻይ ሁኔታዎች ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ከፓናል ውይይቱ በተጓዳኝ የስፖርት ዘርፍን የተመለከተ የፎቶ አውደ ርዕይም ተከፍቷል።