በለውጡ ዓመታት ለአረንጓዴ አሻራ ልማት የተሰጠው ትኩረት የተራቆቱ አካባቢዎችን እየለወጠ ነው- አቶ አሻድሊ ሃሰን

አሶሳ፤ ሰኔ 28/2017(ኢዜአ)፦በለውጡ ዓመታት ለአረንጓዴ አሻራ ልማት የተሰጠው ትኩረት የተራቆቱ አካባቢዎችን እየለወጠ እንደሚገኝ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሃሰን ገለጹ።

በክልሉ እየተከናወነ ያለው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር የህዳሴ ግድብን ከደለል በመከላከል ረገድ ፋይዳው የላቀ መሆኑንም ርዕሰ-መስተዳድሩ ተናግረዋል።

ዛሬ በክልሉ ኡራ ወረዳ ሰልጋ 20 ንዑስ ተፋሰስ ልማት ላይ በተከናወነው የ2017 የአረንጓዴ አሻራ ማስጀመሪያ መርሃ-ግብር ላይ ርዕሰ-መስተዳድሩ እንደገለጹት የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ከተጀመረ በኋላ በአካባቢው ስነ-ምህዳር ተጨባጭ ለውጥ መጥቷል።

በክልሉ እየተከናወነ ያለው ተከታታይ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ከልማትም ባለፈ የህዳሴ ግድብን ከደለል በመከላከል ረገድ ፋይዳው የላቀ መሆኑን ገልጸዋል።


 

በለውጡ ዓመታት በተለይም ለአረንጓዴ አሻራ ልማት በተሰጠው ልዩ ትኩረት በርካታ የተራቆቱ አካባቢዎች እየለሙ መሆኑን አንስተዋል።

ባለፉት ዓመታት የተተከሉ የኢኮኖሚ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች ፍሬ እየሰጡ በመሆኑ የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥና የአካባቢ ጥበቃን በማጠናከር ውጤት መጥቷል ሲሉም ተናግረዋል።

የዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአዲስ አበባ የተጀመረ ሲሆን በክልሎችም በተጠናከረ መልኩ ቀጥሏል።

በመሆኑም በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልልም በዛሬው እለት በይፋ መጀመሩን ተከትሎ የክልሉ ህዝብ በትጋት አረንጓዴ አሻራውን ለማሳረፍ እንዲነሳሳ ርእሰ-መስተዳድሩ ጥሪ አቅርበዋል።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ ባበክር ሀሊፋ፤ በክልሉ አብዛኛው ተፋሰሶች ከህዳሴ ግድብ ጋር የሚያያዙ በመሆናቸው የሚተከሉ ችግኞች ህዳሴ ግድብን ከደለል ለመጠበቅ ፋይዳቸው የጎላ ነው ብለዋል።


 

እስከ አሁን በ47 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ ሲከናወን መቆየቱን የገለፁት ኃላፊው የተፋሰስ ልማት በተከናወነበት አካባቢ ደግሞ ችግኞች በብዛት የሚተከሉ መሆኑን ተናግረዋል።

በችግኝ ተከላ መርሃ-ግብሩ በየደረጃው ያሉ የክልሉ አመራሮች፣ የፀጥታ አካላት፣ ወጣቶች እንዲሁም የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም