የአረንጓዴ አሻራ ልማቱ እንደ ሀገር የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥና ከተረጂነት ለመውጣት ለሚደረገው ጥረት ፋይዳው የላቀ ነው

ጋምቤላ ፤ ሰኔ 28/2017 (ኢዜአ) ፦የአረንጓዴ አሻራ ልማቱ እንደ ሀገር  የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥና ከተረጂነት ለመውጣት ለሚደረገው ጥረት ፋይዳው የላቀ መሆኑን የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አለሚቱ ኡሞድ ገለጹ።

''በመትከል ማንሰራራት'' በሚል መሪ ሀሳብ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአዲስ አበባ በይፋ የተጀመረው የዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በክልሎችም ተጠናክሮ ቀጥሏል።

በዚህም በዛሬው እለት በጋምቤላ የክልሉ ርእሰ መስተዳድር አለሚቱ ኡሞድ፤ በተገኙበት በክልል ደረጃ የአረንጓዴ አሻራ ልማት በይፋ ተጀምሯል።


 

ርዕሰ መስተዳድሯ አሻራቸውን ካኖሩ በኋላ ባስተላለፉት መልእክት የአረንጓዴ አሻራ ልማቱ እንደ ሀገር  የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥና ከተረጂነት ለመውጣት ለተጀመሩ ጥረቶች ጉልህ ድርሻ አለው ብለዋል።

በዚህም መሰረት የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብሩ በክልሉ በተጠናከረ መልኩ መቀጠሉን አንስተው በልማቱ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች በብዛት የሚተከሉ መሆኑን ተናግረዋል።


 

ከመትከልም ባለፈ ለጽድቀታቸው በመንከባከብና በመጠበቅ ለአገልግሎት እንዲበቁ ማድረግ የሁሉም አደራና ሃላፊነት እንዲሆን ርእሰ መስተዳድሯ ጠይቀዋል።

የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ፓል ቱት፤ የአረንጓዴ አሻራ ልማቱ የአየር ንብረት ለውጥ ተጋላጭነትን ለመቀነስና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ገልጸዋል። 

በክልሉ ባለፉት ተከታታይ አመታት በተከናወነው የአረንጓዴ አሻራ ልማት በተፈጥሮ ሃብት ጥበቃና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት አጋዥ መሆኑንም ተናግረዋል። 


 

በዚህ ዓመት ለተከላ ከተዘጋጁት ችግኞች 60 በመቶ የሚሆኑት የአትክልትና ፍራፍሬ ችግኞች መሆናቸውን ጠቁመው ከ7 ሺህ ሄክታር በላይ የተራቆቱ መሬቶችን በስነ-ህይወት የማላበስ እቅድ ተይዟል ብለዋል። 

በዛሬው እለይ በይፋ የተጀመረው ክልል አቀፍ የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ለቀጣይ ሁለት ወራት ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑም ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም