13ኛው የሴቶች አፍሪካ ዋንጫ ዛሬ ይጀመራል 

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 28/2017(ኢዜአ)፦ በሞሮኮ አስተናጋጅነት የሚካሄደው 13ኛው የሴቶች የአፍሪካ ዋንጫ ከዛሬ ጀምሮ ይካሄዳል።

በውድድሩ ላይ 12 ሀገራት በሶስት ምድብ ተከፍለው ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። 

በምድብ አንድ አዘጋጇ ሀገር ሞሮኮ፣ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ሴኔጋል፣ ዛምቢያ ተደልድለዋል።

አልጄሪያ፣ ቦትስዋና፣ ናይጄሪያ እና ቱኒዚያ ያሉበትን ምድብ ሁለት የሞት ምድብ የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል።

በምድብ ሶስት የወቅቱ የውድድሩ አሸናፊ ደቡብ አፍሪካ፣ ጋና፣ ማሊ እና ታንዛንያ ይገኛሉ።

የውድድሩ የመክፈቻ ጨዋታ በአዘጋጇ ሞሮኮ እና ዛምቢያ መካከል ዛሬ ከምሽቱ 5 ሰዓት ላይ 69 ሺህ 500 ተመልካች በሚያስተናግደው ፕሪንስ ሙላይ አብደላ ስታዲየም ይካሄዳል።

ሁለቱ ቡድኖች እርስ በእርስ ሲገናኙ የአሁኑ ለስድስተኛ ጊዜ ነው። ከዚህ ቀደም ባደረጓቸው አምስት ጨዋታዎች ዛምቢያ ሶስት ጊዜ ስታሸንፍ ሞሮኮ አንድ ጊዜ አሸንፋለች። አንድ ጊዜ አቻ ወጥተዋል።

እ.አ.አ በ2023 ቡድኖቹ ባደረጉት ጨዋታ ዛምቢያ ሞሮኮን 6 ለ 2 በሆነ ሰፊ የግብ ልዩነት ያሸነፈችበት ጨዋታ ከፍተኛ ግብ የተቆጠረበት መርሃ ግብር ነው።

ሀገራቱ እ.አ.አ በ2024 በፓሪስ በተካሄደው 33ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ለሴቶች እግር ኳስ ውድድር ለማለፍ ባደረጉት ጨዋታ ዛምቢያ በደርሶ መልስ ውጤት 3 ለ 2 በማሸነፍ በኦሊምፒኩ መሳተፏን አረጋግጣለች።

ካፍ ውድድሩን ለሚያሸንፈው ሀገር የሚሰጠው ሽልማት ከ500 ሺህ ወደ 1 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር  ከፍ ማለቱን አስታውቋል። 


 

በአጠቃላይ ለውድድሩ የ3 ሚሊዮን 475 ሺህ የአሜሪካን ዶላር ሽልማት ማዘጋጀቱን አስታውቋል። የውድድሩ አጠቃላይ ሽልማት መጠንም በ45 በመቶ ከፍ ማለቱን ገልጿል።

የውድድሩን አዲስ ዋንጫ ይፋ ማድረጉ አይዘነጋም። 

13ኛው የሴቶች አፍሪካ ዋንጫ እስከ ሐምሌ 19 ቀን 2017 ዓ.ም ይቆያል። 

የአፍሪካ ዋንጫው እ.አ.አ በ2024 መካሄድ የነበረበት ቢሆንም በ33ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች፣ ከልክ በላይ በተጨናነቀው ዓለም አቀፍ የውድድር ካሌንደር እና ከካፍ ሌሎች ውድድሮች ጋር እንዳይጋጭ በ2025 እንዲካሄዱ መወሰኑ አይዘነጋም። 

ናይጄሪያ ዘጠኝ ጊዜ የአፍሪካ ዋንጫን በማንሳት የበላይነቱን ስትይዝ ኢኳቶሪያል ጊኒ ሁለት ጊዜ እና ደቡብ አፍሪካ አንድ ጊዜ የውድድሩ አሸናፊ ሆነዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም