በክልሉ ባለፉት ዓመታት በተከናወኑ የአረንጓዴ አሻራ ልማት ሥራዎች ዘርፈ ብዙ ለውጦች ተመዝግበዋል-ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር ) - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ ባለፉት ዓመታት በተከናወኑ የአረንጓዴ አሻራ ልማት ሥራዎች ዘርፈ ብዙ ለውጦች ተመዝግበዋል-ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር )

ሼይ ቤንች፤ ሰኔ 28/2017(ኢዜአ)፦በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ባለፉት ዓመታት በተከናወኑ የአረንጓዴ አሻራ ልማት ሥራዎች ዘርፈ ብዙ ለውጦች መመዝገባቸውን ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) ገለጹ።
የዘንድሮ ክልል አቀፍ የአረንጓዴ አሻራ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ዛሬ በቤንች ሸኮ ዞን ሼይ ቤንች ወረዳ ተካሂዷል።
ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንደገለጹት ላለፉት ዓመታት በተከናወኑ የአረንጓዴ አሻራ ልማት ሥራዎች ዘርፈ ብዙ ውጤቶች ተመዝግብዋል።
የአረንጓዴ አሻራ ልማት ሥራ በክልሉ የአየር ጸባይ ለውጥን ለመቋቋም፣ የአፈርና ውሃ ጥበቃን ለማጠናከር እና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ጉልህ አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑን በማሳያነት ጠቅሰዋል።
የአረንጓዴ ልማት ሥራው በክልሉ ያለውን ደን የመጠበቅ እና የመንከባከብ ባህልን በሚያጠናክር መልኩ እየተተገበረ መሆኑን ጠቁመው፣ ይህም ከአረንጓዴ አሻራ ልማት የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማስቀጠል ያስችላል ብለዋል።
የክልሉ ህዝብ ለልማት ሥራው ያለውን ቁርጠኝነት አጠናክሮ በማስቀጠል ለክልሉ ለውጥና ዕድገት ተግቶ እንዲሰራ ጠይቀዋል።
የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር እና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው በበኩላቸው በክልሉ ባለፉት ዓመታት በተተከሉ ችግኞች እየታዩ ያሉ ለውጦችን ለማጠናከር ይሰራል ብለዋል።
እንደ ሃላፊው ገለጻ በስድስት ዙሮች ከተተከሉ የተለያየ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች ውስጥ ከ86 በመቶ በላይ ጸድቀዋል።
ዘንድሮ የቡና፣ የፍራፍሬ እና የደን ዛፍ ችግኞችን ለመትከል ታቅዶ ወደ ተግባር መገባቱንም ገልጸዋል።
የአረንጓዴ አሻራ መርሀግብር የመሬት ለምነትን በማሳደግ፣ አፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራን በማጠናከር ለምርትና ምርታማነት ማደግ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው ያሉት ደግሞ የቤንች ሸኮ ዞን ምክትል ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሀብታሙ ካፍትን ናቸው።
በዞኑ በአረንጓዴ አሻራ ለፍራፍሬ ልማት ትኩረት መሰጠቱ በምግብ ራስን ለመቻል የሚደረገውን ጥረት ያግዛል ብለዋል።
በሼይ ቤንች ወረዳ ጋያሸማ ቀበሌ ዛሬ በይፋ በተጀመረው ክልላዊ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ላይ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች እና የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።