በክልሉ በአረንጓዴ አሻራ የተተከሉ እጽዋቶችን ተንከባክቦ ለውጤት የማብቃቱ ተግባር ይጠናከራል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ በአረንጓዴ አሻራ የተተከሉ እጽዋቶችን ተንከባክቦ ለውጤት የማብቃቱ ተግባር ይጠናከራል

ሐረር ፤ ሰኔ 28/2017 (ኢዜአ)፡- በሐረሪ ክልል በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የተተከሉ እጽዋቶችን ተንከባክቦ ለውጤት የማብቃቱ ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ ገለጹ።
ርዕሰ መስተዳድሩ እና የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች በጀጎል ዙሪያ የተተከሉ እጽዋቶችን የመንከባከብ ስራ አከናውነዋል።
በዚህ ወቅት ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ፤ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አመራር ሰጪነት የተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በክልሉም በመተግበር ባለፉት ዓመታት ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው በርካታ እጽዋቶች መተከላቸውን አስታውሰዋል።
በመርሃ ግብሩ የተተከሉ ችግኞች አካባቢን አረንጓዴ ከማላበስ ባለፈ ውብና ማራኪ እንዲሁም ለነዋሪውና ቱሪስት ምቹ እንዲሆኑ እያስቻለ መምጣቱንም ተናግረዋል።
የተተከሉ እጽዋቶችን በቅርበት በመከታተልና በመንከባከብ ለውጤት የማብቃቱ ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።ይህም ጤናማና ጽዱ ስፍራዎችን ማበልጸግ መሆኑን ጠቁመዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ ፤ ማህበረሰቡም ሆነ ተቋማት የተከሏቸውን ችግኞች የመንከባከብና ውሃ የማጠጣት ስራ በማከናወን የድርሻችንን መወጣታችንን ማጎልበት አለብን ብለዋል።
በቀጣይ ቀናት "በመትከል ማንሰራራት" በሚል መሪ ሃሳብ በክልሉ ከተማና ገጠር ወረዳዎች በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያለው ችግኝ የመትከልና ቀደም ሲል የተተከሉትን የመንከባከብ ስራ እንደሚከናወንም ጠቁመዋል።
በተለይ በመርሃ ግብሩ ላይ በመሳተፍ ቀደም ሲል የተተከሉ እጽዋቶችን ሲንከባከቡ ለቆዩ የፖሊስ አባላት፣ወጣቶችና ሌሎችም የሕብረተሰብ ክፍሎች ምስጋና አቅርበዋል።
ዛሬ ከጠዋቱ 12 ጀምሮ በተከናወነው የተተከሉ እጽዋቶች እንክብካቤ ላይ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ሮዛ ኡመር፣ የክልሉ ካቢኔ አባላት፣የጸጥታ ሃይል፣የመንግስት ተቋማት ሰራተኞችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።