ነፃና ገለልተኛ የዴሞክራሲ ተቋማት ለጠንካራ አገረ-መንግስት ግንባታ ያላቸውን ሚና የበለጠ ለማጉላት ምክር ቤቱ ድጋፉን ይቀጥላል -አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 28/2017 (ኢዜአ)፦ ነፃና ገለልተኛ የዴሞክራሲ ተቋማት ለጠንካራ አገረ-መንግስት ግንባታ ያላቸውን ሚና የበለጠ ለማጉላት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ገለፁ።

ለምክር ቤቱ ተጠሪ የሆኑ የዴሞክራሲ ተቋማት የተቋማዊ ሪፎርም ሥራዎች አፈፃፀም የጋራ መድረክ እየተካሄደ ነው።


 

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ በመድረኩ መክፈቻ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ለዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበር የዴሞክራሲ ተቋማት ጉልህ ሚና እንዳላቸው ገልፀዋል። 

የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች በአግባቡ እንዲከበሩ በሕገ-መንግስቱ መሰረት ነፃና ገለልተኛ የዴሞክራሲ ተቋማት ተቋቁመው እየሰሩ መሆኑንም አስታውሰዋል።

ተቋማቱ ኃላፊነታቸውን በብቃት እንዲወጡም በህግና አደረጃጀት ላይ ያሉ ተግዳሮቶች እንዲስተካከሉ የሪፎርም ስራዎች መሰራታቸውንም ነው የገለፁት።

የዴሞክራሲ ተቋማት ለጠንካራ አገረ-መንግስት ግንባታ ያላቸውን ቁልፍ ሚና የበለጠ ለማሳደግ ምክር ቤቱ በአፈፃፀም ላይ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመፍታት በቁርጠኝነት እንደሚሰራም አረጋግጠዋል።


 

ምክር ቤቱ የተቋማቱን አፈፃፀም በየጊዜው እየገመገመ ህግና አሰራር ላይ ክፍተቶችን ለመሙላት አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል ነው ያሉት።

መገናኛ ብዙሃን የአገርን ሰላም፣ አንድነትና ልማት የሚያጠናክሩ አጀንዳዎችን በማስረፅ የተጣለባቸውን ኃላፊነት በብቃት መወጣት የሚያስችላቸውን ሪፎርም ማድረጋቸውን አመልክተዋል።

በመድረኩ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን፣ የኢትዮጵያ ህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም እንዲሁም የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት፣ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን፣ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽንና የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት  ተቋማዊ የሪፎርም ዕቅድ አፈፃፀም ቀርቦ ውይይት ይደረግበታል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም