የአውሮፓ የእግር ኳስ ኃያላኑ ፒኤስጂ እና ባየር ሙኒክ የሩብ ፍጻሜ መርሃ ግብር ተጠባቂ ነው

አዲስ አበባ ፤ ሰኔ 28/2017 (ኢዜአ)፦ በፊፋ የክለቦች ዓለም ዋንጫ ቀሪ ሁለት የሩብ ፍጻሜ ጨዋታዎች ዛሬ ይደረጋሉ።

የአውሮፓ ሻምፒዮኑ ፒኤስጂ ከባየር ሙኒክ ምሽት 1 ላይ በሜርሴዲስ ቤንዝ ስታዲየም የሚያደርጉት ጨዋታ የዓለምን ትኩረት ስቧል።

ፒኤስጂ በጥሎ ማለፉ ኢንተር ሚያሚን ከፍጹም የጨዋታ ብልጫ ጋር 4 ለ 0 መርታቱ አይዘነጋም።

ተጋጣሚው ባየር ሙኒክ ፍላሚንጎን 4 ለ 2 በማሸነፍ ሩብ ፍጻሜውን ተቀላቅሏል።

“የማይደፈረው ግንብ” እየተባለ በሚል እየተሞካሸ የሚገኘው ፒኤስጂ ጠንካራ የመከላከል አቅም፣ አስደማሚ የመሐል ሜዳ ጨዋታ እና ማራኪ የማጥቃት እንቅስቃሴ መላበሱ አስፈሪ ቡድን አድርጎታል።

ቡድኑ በፊፋ ክለቦች የዓለም ዋንጫ እስከ አሁን በባደረጋቸው አራት ጨዋታዎች 10 ግቦችን አስቆጥሮ አንድ ግብ ብቻ ማስተናገዱ የጥንካሬው ማሳያ ነው።

ምህረት የለሽ የአጥቂ መስመር ተጫዋቾችን የያዘው ባየር ሙኒክ በዘንድሮው ውድድር በርካታ ጎሎች ያስቆጠረ ክለብ ነው። በአራት ጨዋታዎች 16 ግቦችን ከመረብ ሲያገናኝ 4 ግቦችን አስተናግዷል።

ሁለቱ ክለቦች እስከ አሁን በውድድር ጨዋታዎች 14 ጊዜ ተገናኝተው ባየር ሙኒክ 8 ጊዜ ሲያሸንፍ ፒኤስጂ 6 ጊዜ ድል ቀንቶታል።

ባየር ሙኒክ 19 ግቦችን ሲያስቆጥር ፒኤስጂ 15 ጎሎችን ከመረብ ላይ አሳርፏል። 

ቡድኖች እ.አ.አ በ2020 በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ፍጻሜ ተገናኝተው የጀርመኑ ክለብ 1 ለ 0 በማሸነፍ ዋንጫውን ከፍ አድርጓል።

ፒኤስጂ ካለው ወቅታዊ ብቃት አንጻር የማሸነፍ ግምት ቢሰጠውም ባየር ሙኒክ በቀላሉ እጅ ይሰጣል ተብሎ አይጠበቅም።

ከምሽቱ 5 ሰዓት ላይ የመጨረሻው የሩብ ፍጻሜ ጨዋታ በሪያል ማድሪድ እና ቦሩሲያ ዶርትሙንድ መካከል በሜትላይፍ ስታዲየም ይደረጋል።

በጥሎ ማለፉ ሪያል ማድሪድ ጁቬንቱስን 1 ለ 0፣ ቦሩሲያ ዶርትሙንድ ሞንቴሬይን 2 ለ 1 አሸንፈዋል።

ክለቦቹ ከዚህ ቀደም 13 ጊዜ ተገናኝተው ማድሪድ 7 ጊዜ ድል ሲቀናው ዶርትሙንድ 3 ጊዜ አሸንፏል። 3 ጊዜ ደግሞ ነጥብ ተጋርተዋል። እ.አ.አ በ2024 በሻምፒዮንስ ሊግ ፍጻሜ ተገናኝተው ሎስ ብላንኮሶቹ 2 ለ 0 በማሸነፍ ዋንጫውን አንስተዋል።  

በጨዋታው ሲጠበቅ የነበረው የወንድማማቾቹ ጁድ ቤሊንግሀም (ሪያል ማድሪድ) እና  ጆቤ ቤሊንግሃም (ቦሩሲያ ዶርትሙንድ) በተቃራኒ ቡድን የመጫወት ሀገሮች ህልም ሳይሳካ ቀርቷል።

ጆቤ ቤልንግሃም ዶርትሙንድ ሞንቴሬይን ባሸነፈበት ጨዋታ ላይ በውድድሩ ሁለተኛውን ቢጫ ካርድ በመመልከቱ ምክንያት በቅጣት አይሰለፍም።

የሁለቱ ጨዋታ ባለድሎች በግማሽ ፍጻሜው የሚገናኙ ይሆናል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም