ቼልሲ ግማሽ ፍጻሜውን ተቀላቀለ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 28/2017 (ኢዜአ)፦  በፊፋ የክለቦች ዓለም ዋንጫ የሩብ ፍጻሜ ሁለተኛ ጨዋታ ቼልሲ ፓልሜራስን 2 ለ 1 አሸንፏል።

ትናንት ከእኩለ ሌሊት በኋላ  በሊንከን ፋይናንሻል ፊልድ ስታዲየም በተደረገው  ጨዋታ ኮል ፓልመር እና የፓልሜራስ ግብ ጠባቂ ዌቨርተን በራሱ ግብ ላይ የማሸነፊያ ጎሎቹን አስቆጥሯል።

እስቴቫኦ ዊሊያን ለፓልሜራስ ብቸኛውን ጎል ከመረብ ላይ አሳርፏል።

በጨዋታ ቼልሲ በኳስ ቁጥጥር እና የግብ እድሎችን በመፍጠር ከተጋጣሚው ተሽሎ ተገኝቷል።

በተለይም በሁለተኛው አጋማሽ ለተመልካች አዝናኛ እና ሳቢ የሆነ የጨዋታ እንቅስቃሴ ለማየት ተችሏል።

ወደ ቼልሲ የተዘዋወረው እስቴቫኦ ዊሊያን በፓልሜራስ ማልያ የመጨረሻ ጨዋታውን አድርጓል።

ቼልሲ ግማሽ ፍጻሜ የገባ ሁለተኛ ቡድን ሆኗል። ከፍሉሜኔንሴ ጋር ማክሰኞ ሐምሌ 1 ቀን 2017 ዓ.ም ለፍጻሜ ለማለፍ ይፋለማል።

ፍሉሜኔንሴ ትናንት ማምሻውን አል ሂላልን 2 ለ 1 በማሸነፍ ግማሽ ፍጻሜውን ተቀላቅሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም