ቀጥታ፡

የኢትዮጵያዊያን የዴሞክራሲ እሴቶች ልምምድ የችግር መፍቻ ቁልፍ አለመሆን "ኢትዮጵያዊ ዴሞክራሲ ፍለጋ" መጽሐፍ እንዲወለድ ሆኗል-ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ሰኔ 27/2017(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያዊያን የዴሞክራሲ እሴቶች ልምምድ በዓለም አቀፍ ደረጃ ማጣቀሻ ያለመሆንና በችግር መፍቻ ቁልፍነት ያለመታየት "ኢትዮጵያዊ ዴሞክራሲ ፍለጋ" መጽሐፍ እንዲወለድ መንስኤ መሆኑን የመጽሐፍ ጸሀፊ ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር) ገለጹ።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር) የተጻፈ "ኢትዮጵያዊ ዴሞክራሲ ፍለጋ" መጽሐፍ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ራስ መኮንን አዳራሽ ተመርቋል።

በሥነ-ስርዓቱ ላይ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ሃላፊና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ፣ የፌዴራልና የክልሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሀላፊዎች እና ጥሪ የተደረገላችው እንግዶች ተገኝተዋል።

"ኢትዮጵያዊ ዴሞክራሲ ፍለጋ"ደራሲ ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር)፤ ኢትዮጵያዊያን በዓለም ላይ አስደናቂ ባህል፣ወግ፣እሴትና ጥበብ ያለን ማህበረሰቦች ነን ብለዋል።

ይህ አስደናቂ የኢትዮጵያዊያን ፍልስፍና ዓለም አቀፋዊ አለመሆን ውስጣዊ ጥያቄን ፈጥሮባቸው እንደቆየ ገልጸዋል።

ዓለም አቀፍ የፍልስፋና ምሁራን እንደሚያነሱት የኢትዮጵያ ፍልስፍናዎች ለምን ዓለም አቀፍ አጀንዳና ማጣቀሻዎች መሆን አቃታቸው የሚለው ለመጽሐፉ መወለድ መነሻ ምክንያት እንደሆናቸው አንስተዋል።

የማውቃት፤ያሳደገችኝ፤ያስተማረችኝና ሁላችንም ለወግና ለማዕረግ ያበቃችን የኢትዮጵያ ዕውነት ምንድን ነው የሚለውም በማሰብ ኢትዮጵያን ያልተረዳንላትና ያላወቅንላት የሚለው መሰረታዊ ጉዳይም ሌላኛው የመጽሐፉ መነሻ ሃሳብ መሆኑን ተናግረዋል።

እንደሀገር ያለፍንባቸው መንገዶችና ያልቀሰምናቸው ትምህርቶች፣ ትናንት ያባከናቸውና ያመለጡ ዕድሎች ምንነትም በመጽሐፉ መዳሰሱን አስረድተዋል።

የተፈጠሩ መሻኮቶችና የመከኑ ትውልዶች፣ባለመግባባትና ባለመወያየት የጨለሙ ተስፋዎች ምክንያትና ምንነት በመጽሐፉ እንደተመላከቱ አስረድተዋል።

ኢትዮጵያ እንደዘበት የዘነጋቻቸው ጥበቦችና ዕውቀቶች ለሀገር ሃብት አቅም አለመሆናቸውም መጽሐፉ በቁጭት የሚዳስሳቸው ጉዳዮች መሆናቸውን አብራርተዋል።

ባለፉት የለውጥ ዓመታት የተፈጠረው ምቹ ሀገራዊ ድባብም እንደሳቸው ያሉ በመንግስትና ፓርቲ ስራ የሚሰሩ አካላት ብቻ ሳይሆን ምሁራን መፃፍ፣መነጋገር፤መወያየትና ሀገራዊ ጉዳዮችን በሰለጠነ መንገድ ሃሳባቸውን የሚያዋጡበት ምህዳር መፈጠሩም ለመጽሐፉ ውልደት አንዱ ቁልፍ ጉዳይ መሆኑን አስረድተዋል።

በኢትዮጵያ በብዛት የካበተ ዕውቀትና እሴት እያለ እንደሌለ በመቁጠር ለኢትዮጵያዊ ጥያቄና ምላሾች በዜጎቿ እጅ እንጠቀም የሚል ሀገራዊ ፍልስፍና እና እሳቤ መወለዱንም አስረድተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድም (ዶ/ር) የዚሁ ፍልስፍና እና እሳቤ ግንባር ቀደም መሪ በመሆን መጽሐፉ እንዲወለድ ሆኗል ብለዋል።

የመጽሐፉ መወለድም የውስጥን ቁጭትና ምኞት፣የተስፋና ምናብ ጉዟቸውን በማሳረፍ በግላቸውና እንደማህበረሰቡ የተመጣበትና የቀጣይ ጉዞ መንገድ ላይ የኢትዮጵያን ዕውነት ለመግለጽ ምልከታና አረዳዳቸውን ያሳረፉበት መሆኑን ገልጸዋል።

ዋነኛ ዓላማውም ከትናንት በመማር ዛንና ነገን የተሻለ በማድረግ ቀጣዮ ትውልድ የተሻለች ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ማስረከብ መሆኑን አስረድተዋል።

"ኢትዮጵያዊ ዴሞክራሲ ፍለጋ"መፅሐፍ ገቢም በጎፋ ዞን በደረሰው የመሬት መንሸራተት አደጋ ለተጎዱ ወገኖች ትምህርት ቤትና የመሰረተ ልማት ግንባታ እንዲውል ለግሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም