የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የብድር ስምምነቶችን አጸደቀ - ኢዜአ አማርኛ
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የብድር ስምምነቶችን አጸደቀ
አዲስ አበባ፤ሰኔ 27/2017(ኢዜአ)፦የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባካሄደው ሁለተኛ ልዩ ስብሰባው ሁለት የብድር ስምምነቶችን አጽድቋል።
ምክር ቤቱ በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ እና በዓለም አቀፍ የልማት ማህበር መካከል ለሁለተኛው ዘላቂ እና ሁሉን አቀፍ የእድገት ልማት ፖሊሲ ማስፈፀሚያ የተደረገው የብድር ስምምነት ላይ ከተወያየ በኋላ በሙሉ ድምጽ አጽድቋል።
የብድሩን አስፈላጊነት እና ዓላማ የመንግስት ረዳት ተጠሪ ሚኒስትር ዴኤታ መሰረት ኃይሌ አቅርበዋል።
በብድር የተገኘው ገንዘብ መንግሥት የጀመራቸውን የሪፎርም ሥራዎችን ለመደገፍ እንዲቻል እና የፌደራል መንግሥትን የ2018 በጀት በቀጥታ ለመደገፍ እንደሚውል ተናግረዋል።
ብድሩም ከወለድ ነጻ እና በረጅም ዓመታት የሚከፈል መሆኑን አስረድተዋል።
ረዳት ተጠሪ ሚኒስትር ዴኤታ መሰረት፥ ብድሩ እየተከናወኑ ያሉ የተለያዩ ስራዎችን ያለችግር እንዲጠናቀቁ የሚያስችል ነው ብለዋል።
የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ በበኩላቸው የተገኘው ገንዘብ የ2018 በጀትን ፋይናንስ ለማድረግ እና የተጀመሩ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን ለማጠናከር ያለመ መሆኑን አስረድተዋል።
መንግስት ባለፉት ዓመታት የተገበረው የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ጠንካራ ዕድገት ማምጣቱን ገልጸዋል።
ፕሮግራሙ መንግስት በተለያዩ ዘርፎች የጀመራቸውን የማሻሻያ እርምጃዎች ለመደገፍ የቀጥታ በጀት ድጋፍ በማድረግ ቀጣይነት ያለው ሁሉን አቀፍ የኢኮኖሚ እድገት እንዲኖር ያግዛል ብለዋል።
በተሟላ ማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ደግሞ የገቢ አሰባሰብን በማሳደግ፣ ዘመናዊ የገንዘብ ፖሊሲ ተግባራዊ በማድረግ ዋጋ ንረትን ማረጋጋት፣ ለረጅም ጊዜ ስር ሰዶ የቆየውን የውጭ ምንዛሪ እጥረት ችግር በመፍታት እና የፋይናንስ ዘርፉ ጤናማ እንዲሆን ማድረግ ተችሏል ብለዋል።
የዓለም ባንክ የመንግሥትን የኢኮኖሚ ማሻሻያ እርምጃዎች ለመደገፍ ለቀጥታ በጀት ድጋፍ የሚሆን የ1 ቢሊዮን ዶላር በእርዳታና በብድር መልክ ለኢትዮጵያ መንግስት መስጠቱን ገልጸዋል።
ከዚህ ውስጥ 350 ሚሊዮን ዶላር በብድር እና 650 ሚሊዮን ዶላር ደግሞ በእርዳታ ወይም በድጋፍ የተሰጠ መሆኑን ገልጸዋል።
ለፍጥነት መንገድ ልማት ድጋፍ ፕሮጀክት ከዓለም አቀፍ የልማት ማህበር ለባቱ-አርሲ ነጌሌ የፍጥነት መንገድ ግንባታ ተጨማሪ 37 ሚሊየን ዶላር ብድር መገኘቱን ገልጸዋል።
የምክር ቤቱ አባላት በሰጡት አስተያየት የተገኘው ብድርና ድጋፍ ለሀገሪቱ ቀጣይነት ላለው እድገት አስተዋፅኦ ያለው መሆኑን ተናግረዋል።
የተገኘውን ገንዘብ በአግባቡ ለታለመለት ዓለማ ማዋል እንደሚገባና ጠንካራ ክትትል እንደሚደረግ አሳስበዋል።
በሌላ በኩል ምክር ቤቱ በኢትዮጵያ እና በናይጄሪያ መንግሥታት መካከል የዲፕሎማቲክ ወይም ኦፊሻል የአገልግሎት ፓስፖርት ለያዙ የሁለቱ ሀገራት ዜጎች ቪዛን ለማስቀረት የሚያስችል ስምምነትን አጽድቋል።
ስምምነቱ በሁለቱ አገሮች መካከል ያለውን የሁለትዮሽ ግንኙነት ለማጠናከር እና የፖለቲካ ትብብርን ከፍ ለማድረግ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ተገልጿል።
በመጨረሻም ምክር ቤቱ የፌዴራል የገቢ ግብር አዋጅን ለማሻሻል የቀረበ ረቂቅ አዋጅን መርምሮ በዝርዝር ለሚመለከተው የፕላን በጀትና ፋይናንስ ቋሚ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቷል።
በተመሳሳይ የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ-ምግባር አዋጅን ለማሻሻል የቀረበ ረቂቅ አዋጅን መርምሮ ለዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቷል።