በክልሉ ለአረንጓዴ አሻራ ልማት መጠናከር ህብረተሰቡ ሲያከናውን የቆየውን ተግባር ማጠናከር አለበት

ሚዛን አማን፣ሰኔ 27/2017 (ኢዜአ)፦በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ለአረንጓዴ አሻራ ልማት መጠናከር ህብረተሰቡ በቁርጠኝነት ሲያከናውን የቆየውን ተግባር አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተገለጸ።

የክልሉ የ2017 ዓ.ም የክረምት ወራት የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ነገ በይፋ እንደሚጀመር ተመላክቷል።

በክልሉ ውስጥ የሚገኙ የብሔራዊና የክልል ሚዲያ ተቋማት አመራሮችና ባለሙያዎች ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ጋር በመሆን በሚዛን አማን ከተማ ችግኝ በመትከል አረንጓዴ አሻራቸውን አኑረዋል።

የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ምክትል ኃላፊ ወይዘሮ በረከት እዮብ በእዚህ ወቅት እንደገለጹት፣ የዘንድሮ የክልሉ የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር ነገ በይፋ የሚጀመር ሲሆን አስፈላጊው ዝግጅትም ተደርጓል።

በዘንድሮ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች እንደሚተከሉም አስታውቀዋል።

ለዚህም የችግኝና የጉድጓድ ቁፋሮ ዝግጅት ተደርጓል ያሉት ወይዘሮ በረከት፣ በዛሬው እለትም የመገናኛ ብዙሀንና የኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች ችግኝ በመትከል አረንጓዴ አሻራቸውን ማሳረፋቸውን ተናግረዋል።

በክልሉ ለአረንጓዴ አሻራ ልማት መጠናከር ህብረተሰቡ በቁርጠኝነት ሲያከናውን የነበረውን ተግባር በቀጣይም አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ወይዘሮ በረከት ገልጸዋል።

በክልሉ ባህል ሆኖ የቆየውን የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ለማስቀጠልና የራስን አሻራ አክሎ ለቀጣይ ትውልድ ለማስተላለፍ በሚደረግ ጥረት ህብረተሰቡ ችግኝ በመትከልና በመንከባከብ ሲያደርግ የቆየውን ተሳትፎ እንዲያጠናክርም አሳስበዋል።

ዛሬ በተካሄደው የመገናኛ ብዙሀን ባለሙያዎች የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ላይ የተሳተፉት የደቡብ ሬዲዮና ቴሌቭዥን ድርጅት ሚዛን ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ አቶ ትዕዛዙ ኬንጫ፣ ከዘገባ ሥራ ባሻገር አረንጓዴ አሻራችንን በማሳረፍ ልማቱን ለማጠናከር በችግኝ ተከላው ላይ መሳተፋቸውን ገልጸዋል።

በጋራ ችግኝ በመትከላቸው ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸው፣ ህብረተሰቡ የችግኝ ተከላ ተሳትፎውን በማጠናከር የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር ግብን ለማሳካት መረባረብ ይኖርበታል ብለዋል።

የመገናኛ ብዙሀን ባለሙያዎች ችግኝ በመትከል የአረንጓዴ አሻራቸውን በማሳረፍ የዜግነት ግዴታቸውን እንዲወጡ መደረጉ መልካም ነው ያለው ደግሞ የቤንች ሸኮ ዞን ኮሙኒኬሽን ባለሙያ ተዘራ ጥላሁን ነው።

መሰል መርሃ ግብሮች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ገልጾ፣ "የክልሉ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ቢሮ በዚህ መልኩ አቀናጅቶ ችግኝ እንድንተክል ማድረጉ ይበረታታል" ብሏል።

በሚዛን አማን ከተማ በተካሄደው የመገናኛ ብዙሀን ተቋማት የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ላይ የተለያዩ መገናኛ ብዙሀን ባለሙያዎች፣ የኮሙኒኬሽን ሥራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።

"በመትከል ማንሰራራት" በሚል መሪ ቃል ክልል አቀፍ የአረንጓዴ አሻራ ማስጀመሪያ መርሀግብር ነገ በቤንች ሸኮ ዞን ሸይ ቤንች ወረዳ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት እንደሚካሄድ ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም