ቀጥታ፡

የህዳሴ ግድብ ስኬት ከተባበርን የትኛውንም ለውጥ ማስመዝገብ እንደምንችል ማሳያ ነው-የአዲስ አበባ ነዋሪዎች

አዲስ አበባ፤ሰኔ 27/2017(ኢዜአ)፦የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ስኬት ከተባበርን የትኛውንም ለውጥ ማስመዝገብ እንደምንችል ማሳያ ነው ሲሉ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 42ኛ መደበኛ ስብሰባውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት ትናንት አካሄዷል፡፡

በዚሁ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

በማብራሪያቸው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የማጠናቀቂያ ምዕራፍ ላይ መድረሱንና በመጭው መስከረም እንደሚመረቅ ተናግረዋል፡፡

ግድቡ ለሱዳን እና ግብፅ በረከት መሆኑን ጠቅሰው፥ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ልማት ልማታቸው ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ኢነርጂ ደግሞ ለሁሉም ጎረቤት አገራት የሚዳረስ ነው ብለዋል።

ኢዜአ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ የሰጡትን ማብራሪያ መነሻ በማድረግ የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን አነጋግሯል፡፡

ነዋሪዎቹ በሰጡት አስተያየት የህዳሴ ግድብ ግንባታ ለዚህ ደረጃ መድረሱ የኢትዮጵያውያን የአንድነታችን ማሳያ ነው ብለዋል፡፡

የመዲናዋ ነዋሪ የሆነው ከሚል አህመዲን ለፕሮጀክቱ ስኬት የበኩሉን አስተዋጽኦ ማበርከቱን በመግለጽ ፤ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምክር ቤቱ ያበሰሩት መልዕክት ለኢትዮጵያ ትልቅ ስኬት ነው ብሏል።

ሌላኛዋ አስተያየት ሰጪ መንበረ ግዛው በበኩሏ፤ የአንድነት ማሳያ የሆነው የህዳሴ ግድብ ለኢኮኖሚው የሚያስፈልገውን ሃይል በበቂ ደረጃ በማቅረብ ለበርካታ ወጣቶች የስራ እድል እንዲፈጠር ያስችላል ብላለች፡፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ አስተማማኝና ዘላቂ የሆነ የኤሌክትሪክ ሃይል ለህብረተሰቡ በፍትሃዊነት ተደራሽ እንዲሆን ያስችላል ሲል የገለጸው ደግሞ ፍቃዱ ደጀኔ ነው፡፡

ሌላኛው አስተያየት ሰጪ ተረፈ ዘለቀ ግድቡ በሙሉ አቅሙ ወደ ስራ ሲገባ ለሀገር ኢኮኖሚ ዕድገት ካለው ከፍተኛ አስተዋጽኦ ባለፈ ለቀጠናዊ የሃይል ትስስር የማይተካ ፋይዳ እንደሚኖረው ተናግሯል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም