ቀጥታ፡

በጎንደር ከተማ በቀጣዮቹ ሶስት ወራት የልማት እቅዶች ህዝቡን በስፋት ባሳተፈ መልኩ ይከናወናል

ጎንደር፤ሰኔ 27/2017 (ኢዜአ)፦በጎንደር ከተማ የቀጣዮቹ ሶስት ወራት የልማት፣ የሰላምና የመልካም አስተዳደር እቅዶች ህዝቡን በስፋት ባሳተፈ መልኩ እንደሚከናወኑ የከተማ አስተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ቻላቸው ዳኘው ተናገሩ፡፡

ለከተማው አመራር በቀጣይ ሶስት ወራት የልማት፣የሰላምና የመልካም አስተዳደር ስራዎች እንዲሁም የአረንጓዴ አሻራ እና ሌሎች ተግባራት የእቅድ ትውውቅ መድረክ ዛሬ ተካሂዷል፡፡

በመድረኩ ላይ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው አቶ ቻላቸው ዳኘው እንደተናገሩት፥ በ2017 በጀት አመት የኮሪደር ልማትን ጨምሮ በከተማው የተከናወኑ ዘርፈ ብዙ የልማት ተግባራት የህዝቡን የልማት ጥያቄ ምላሽ የሰጡ ናቸው፡፡


 

በቀጣዮቹ ሶስት ወራት አመራሩ ግንባር ቀደም በመሆን መላው የከተማውን ህዝብ በንቅናቄ በማሳተፍ የልማት እቅዱን ተፈጻሚ ማድረግ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

በመርሃ ግብሩ ከ20 ሺህ በላይ የከተማውን ወጣቶች በማሳተፍ የእቅመ ደካሞች የቤት እድሳትና ግንባታ ስራ እንዲሁም በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ደግሞ ችግኞችን የመትከል ስራ ይከናወናል ብለዋል፡፡

የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር፤ የኢትዮ ኮደርስ ስልጠና፤ የፋይዳ ዲጅታል መታወቂያ ምዝገባ፤የወጣቶች ስራ እድል ፈጠራ እንዲሁም ገበያ ማረጋጋት ስራዎች በክረምቱ ወራት የሚከናወኑ ዋና ዋና ተግባራት መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡

በኢንቨስትመንት ዘርፍ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄን አጠናክሮ የማስቀጠል እንዲሁም በትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ የማሻሻል ስራዎች በትኩረት ይከናወናሉ ብለዋል፡፡

የአካባቢ ጥበቃ ተግባራትን አጠናክሮ በማስቀጠል በክረምቱ ወራት የጎርፍ አደጋዎችን ለመከላከል የሚያስችሉ ስራዎች እንደሚከናወኑም ጠቁመዋል፡፡

በብልጽግና ፓርቲ የከተማ አስተዳደሩ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ተስፋ መኮንን በበኩላቸው፥ ለእቅዶች መሳካት አመራሩ ሚናውን ይበልጥ ለመወጣት ዝግጅት ማድረግ እንደሚጠበቅበት አስረድተዋል፡፡

በ2017 በጀት አመት የተከናወኑ የሰላም፣ የልማትና የመልካም አስተዳደር ተግባራት የፓርቲው ጉባኤ ባስቀመጣቸውና ባሳለፋቸው የውሳኔ አቅጣጫዎች መሰረት በመተግበራቸው ውጤት ማስመዝገብ መቻሉን ተናግረዋል፡፡

የከተማውን ሰላም በዘላቂነት በማረጋገጥ ለልማት ስራዎች ምቹ የሰላም አውድ በመፍጠር ረገድ የጸጥታ መዋቅሩ በርካታ ተግባራት ማከናወኑን የገለጹት ደግሞ የከተማ አስተዳደሩ ሰላምና ጸጥታ መምሪያ ሃላፊ አቶ አለልኝ አለም ናቸው፡፡

የጸጥታ መዋቅሩ ግዳጅ የመፈጸም ብቃቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን ጠቁመው፥ ህገወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውርንና ሌሎች ወንጀሎችን በመቆጣጠር ረገድ ህግ የማስከበር ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አስረድተዋል፡፡

በከተማው በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች በተሳተፉበት የእቅድ ትውውቅ ላይ በቀጣዮቹ ሶስት ወራት የሚከናወኑ ዋና ዋና ተግባራት ሰነድ ቀርቦ ውይይት የተካሄደ ሲሆን የተግባር አፈጻጸም የጋራ አቅጣጫም ተቀምጧል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም