"ኢትዮጵያዊ ዴሞክራሲ ፍለጋ" መጽሐፍ የዘመናት የዴሞክራሲ ፍለጋ ህልምን የሚዳስስ የዕውቀት ብርሃን ነው - ኢዜአ አማርኛ
"ኢትዮጵያዊ ዴሞክራሲ ፍለጋ" መጽሐፍ የዘመናት የዴሞክራሲ ፍለጋ ህልምን የሚዳስስ የዕውቀት ብርሃን ነው
አዲስ አበባ፤ሰኔ 27/2017(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያዊ ዴሞክራሲ ፍለጋ" መጽሐፍ የኢትዮጵያ ህዝብን የዘመናት የዴሞክራሲ ፍለጋ ህልም የሚዳስስ የዕውቀት ብርሃን መሆኑን በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ ገለጹ።
በመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትሩ ተስፋዬ በልጅጌ(ዶ/ር) የተጻፈው "ኢትዮጵያዊ ዴሞክራሲ ፍለጋ" መጽሐፍ ዛሬ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣ የፌደራል እና የክልል ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት ተመርቆ ለንባብ በቅቷል።
በምርቃት መርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ መጽሐፉ ከኢትዮጵያዊ ባህል ወርቃማ የእሴት ቁልፎችን የያዘ መሆኑን ገልጸዋል።
በቀጣይም በሀገር እና በተቋማት ግንባታ ሂደት በማጣቀሻነት እንደሚያገለግል ተናግረዋል።
የመፀሐፉ ፀሐፊ የሆኑት ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር) የመንግስት የስራ ኃላፊነታቸውን በብቃት የሚወጡ፣በቅርቡም የሦስተኛ ዲግሪያቸውን ይዘውና መጽሐፉን አጠናቀው ለተደራሲያን ማቅረባቸው ጊዜያቸውን በአግባቡ እንደሚጠቀሙ ያሳያል ብለዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን (ዶ/ር) አርዓያነት በመከተል መጽሐፍ የማዘጋጀት ሂደት ለሁሉም የስራ ኃላፊዎች ትምህርት የሚሰጥ መሆኑን አብራርተዋል።
የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ሂደት ለትውልዶች ሲተላለፍ የቆየ ህዝባዊ ጥያቄ ነው ያሉት አቶ አደም፤ ሁሉም ሲያውጠነጥነው የቆየና እስካሁንም የተሟላ ምላሽ ያልተገኘለት መሆኑን አንስተዋል።
መፅሐፉ ስለዴሞክራሲ የተከተልነውን አካሄድ እንድናጤንና በትኩረት እንድንሰራ የሚያግዘን ነው ብለዋል።
በዴሞክራሲ ላይ የሚፈለገውን ለውጥ ለማምጣት ሀገር በቀል እሴቶችን ከዘመናዊ አስተሳሰብ ጋር ማጣጣም፣ዴሞክራሲ የሂደትና የውጤት ገጽታዎች እንዳሉት መረዳት፣ኋላቀር የፖለቲካ ባህልን መቀየርና ሚዛናዊነትን ማጎልበት እንዲሁም የዴሞክራሲ ተቋማት ማጠናከር እንደሚገባ ገልጸዋል።
"ኢትዮጵያዊ ዴሞክራሲ ፍለጋ" መፅሐፍ ለቀጣዩ ትውልድ የተሻለች ኢትዮጵያን ማስረከብ የሚያስችል ምህዳር ለመፍጠር ጥብቅ ንድፈ ሀሳቦችን ማቅረቡን ተናግረዋል።
መጽሐፉ ለኢትዮጵያ ህዝብ የዘመናት የዴሞክራሲ ፍለጋ ህልም የዕውቀት ብርሃን መሆኑንም አስረድተዋል።