በዘንድሮው የክረምት ወቅት የኃይል መቆራረጥ እንዳይገጥም በቂ ዝግጅት ተደርጓል-የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት - ኢዜአ አማርኛ
በዘንድሮው የክረምት ወቅት የኃይል መቆራረጥ እንዳይገጥም በቂ ዝግጅት ተደርጓል-የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት
አዲስ አበባ፤ሰኔ 27/2017(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በዘንድሮው የክረምት ወቅት የኃይል መቆራረጥ እንዳይገጥም በቂ ዝግጅት ማድረጉን ገለፀ።
አገልግሎቱ በክረምት ወቅት የኃይል መቆራረጥን ለመቀነስ የተሰሩ የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል።
የአገልግሎቱ የኔትወርክ ኢንፍራስትራክቸርና ኦፕሬሽን ኤክሰለንስ ዳይሬክተር ፈሪድ አብዱልሰላም እንዳሉት፥ የክረምት ዝናብና የአየር ፀባይን ተከትሎ የኃይል መቆራረጥ ችግሮችን ለመፍታት ዝግጅት ተደርጓል።
አገልግሎቱ ካለፉት ዓመታት ልምድ በመነሳት በክረምት የሚኖረውን የኃይል መቆራረጥ ለመቀነስ በጥናት ላይ የተመሰረቱ የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን አከናውኗል።
በጥናቱ መሰረት 56 በመቶ የሚጠጉ ችግሮችን ማስተካከል፣ያረጁ መስመሮችና ምሰሶዎችን የመቀየር፣ከኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ጋር ንክኪ ያላቸውን ዛፎች የማንሳት ስራ መከናወኑን አስታውቀዋል።
በተገባደደው በጀት ዓመት የኃይል መቆራረጥን ዜሮ የማድረግ እቅድ ተይዞ ሲሰራ መቆየቱን ጠቅሰው፥ በዚህም የኃይል መቆራረጥ ምጣኔውን በሚታይ መልኩ መቀነስ መቻሉን ተናግረዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ በ152 መካከለኛ መስመሮች እና መስመሮችን በሚሸከሙ 59 ሺህ 48 ምሰሶዎች ላይ ጥልቅ ፍተሻ መደረጉንም ገልጸዋል።
በዚህም ከባድና ቀላል የኃይል መቆራረጥ መንስኤ የሆኑ የግኝት ነጥቦች መለየታቸውን ነው ያነሱት፡፡
የአገልግሎቱ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አንዋር አብራር በበኩላቸው፥ ተቋሙ በሀገር አቀፍ ደረጃ በሚከናወነው የዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር 100 ሺህ ችግኞችን ለመትከል ማቀዱን ጠቅሰዋል።
አገልግሎቱ ችግኞቹን የሚተክለው ከኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ጋር ንክኪ በመፍጠር የኃይል መቆራረጥ እንዲፈጠር ሲያደርጉ የነበሩና የተቆረጡ ዛፎችን ለመተካት እንዲሁም ሀገራዊ የአረንጓዴ አሻራ ሚናውን ለመወጣት ነው ብለዋል።
ህብረተሰቡ የወደቁና የተንጠለጠሉ የኤሌክትሪክ ገመዶች ወይም ሌሎች ብልሽቶች ሲያጋጥሙት በአገልግሎቱ ነፃ የስልክ መስመር 905 በፍጥነት እንዲያሳውቅ ጥሪ ቀርቦለታል።