የኤሌክትሮኒክስ ግዢ በዘርፉ የነበረውን ብልሹ አሰራር ከመቀነስ ባለፈ ወጪና ጊዜን መቆጠብ አስችሏል

አዳማ፤ሰኔ 27/2017(ኢዜአ)፦የኤሌክትሮኒክስ ግዢ በዘርፉ የነበረውን ብልሹ አሰራር ከመቀነስ ባለፈ ወጪና ጊዜን መቆጠብ ማስቻሉን የመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ መሰረት መስቀሌ ገለፁ።

የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች የባለስልጣኑን የሪፎርም ስራዎች ለህብረተሰቡ በማሳወቅና ግንዛቤ በመፍጠር ሙያዊ እገዛ በሚያደርጉበት ሁኔታ ላይ ውይይት ተካሄዷል።


 

ዋና ዳይሬክተሯ በወቅቱ እንደገለፁት፥ የኤሌክትሮኒክስ ግዥ ስርዓት ተግባራዊ ከተደረገ ወዲህ በዘርፉ ውጤቶች እየተገኙ ነው።

ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ በእስካሁኑ አፈጻጸምም 169 ባለበጀት የፌዴራል መስሪያ ቤቶችና 93 ቅርንጫፎቻቸው ወደ ኤሌክትሮኒክስ ግዢ ስርዓት መግባታቸውን ገልጸዋል።

የግዢ እቅዶቻቸውን በኤሌክትሮኒክስ በማቅረብ ረገድ አበረታች እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን ገልጸው፥ በተለይ የዕቃና አገልግሎት ግዢ ጥያቄዎች በኤሌክትሮኒክስ ሂደት ብቻ እየቀረቡ ናቸው ብለዋል።

ስርዓቱ የመረጃ ግልጽነት በመፍጠር ብልሹ አሰራሮችን ለማስወገድ ከማገዙም በላይ ለክትትልና ቁጥጥር ስራ አመቺ እንዲሆን መደረጉን ተናግረዋል።


 

በተጨማሪም ስርዓቱ ጊዜና አስተዳደራዊ ወጪ ቆጣቢ አሰራር እውን ከማድረጉም ባለፈ የተጭበረበሩ ሰነዶችንና ብልሹ አሰራሮችን የቀነሰ እንዲሁም የህግ ተፈፃሚነትን ያረጋገጠ መሆኑንም አስረድተዋል።

ቴክኖሎጂው ከሰው ንክኪ ነፃ በመሆኑ ስህተቶችን በማስቀረት ረገድ ትልቅ ጠቀሜታ ያለው መሆኑን ጠቅሰው፥ የፌዴራል ባለበጀት መስሪያ ቤቶች በኤሌክትሮኒክስ ግዥ ሂደት ብቻ መጠቀም አለባቸው ብለዋል።

የውል አስተዳደር፣የአቤቱታ አቀባበል፣የሚወገዱ ንብረቶችን ጨምሮ ሁሉንም አገልግሎቶች ኦንላይን ለማድረግ በ26 ዋና ዋና መስኮች ላይ የማሻሻያ ሪፎርም በማድረግ የዲጂታል አሰራር ዝርጋታ መከናወኑን ጠቅሰዋል።

ተቋሙ የዲጂታል አሰራሮችን ተደራሽ በማድረግ በተለይ ተቋማዊ አቅምን ለመገንባት ባለድርሻ አካላት ባሉበት ቦታ የቀጥታ ስልጠና ለመስጠት የሚያስችለውን አሰራር መዘርጋቱን ገልጸዋል።

ባለስልጣኑ ስርዓቱን ወደ ክልሎችና የከተማ መስተዳድሮች ለማውረድ ከባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እየሰራ መሆኑን ገልጸው፥ የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎችም በባለስልጣኑ እየተከናወኑ ያሉ የሪፎርም ስራዎችን በማስተዋወቅ ረገድ ሙያዊ ድጋፋቸውን እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

በመድረኩ ላይ ከተለያዩ የሚዲያ ተቋማት የተወጣጡ አመራሮች፣የዘርፉ የስራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ተሳታፊ ሆነዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም