ኢትዮጵያ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን ለመከላከል ከኢንተርፖል ጋር ያላትን ትብብር አጠናክራ ትቀጥላለች-ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን ለመከላከል ከኢንተርፖል ጋር ያላትን ትብብር አጠናክራ ትቀጥላለች-ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ
አዲስ አበባ፤ሰኔ 27/2017(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን ለመከላከል ከኢንተርፖል ጋር ያላትን ትብብር አጠናክራ ትቀጥላለች ሲሉ የኢፌዴሪ ፕሬዳዝንት ታዬ አፅቀሥላሴ ገለጹ።
የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ የኢንተርፖል ፕሬዝዳንት ሜጀር ጀነራል አህመድ ናስር አል-ራይሲን በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።
ፕሬዝዳንት ታዬ ኢንተርፖል በዓለም አቀፍ ደረጃ በፖሊስ ተቋማት መካከል ትብብርን በማመቻቸት እየተጫወተ ያለውን ሚና አድንቀዋል፡፡
ኢትዮጵያ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን ለመከላከል ከኢንተርፖል ጋር ያላትን ትብብር አጠናክራ እንደምትቀጥልም ፕሬዝዳንቱ አረጋግጠዋል።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ውይይቱን በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያ፥ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ኢትዮጵያ ለዓለም አቀፍ ደህንነት ያላትን ጽኑ ቁርጠኝነት ለኢንተርፖል ፕሬዝዳንት አረጋግጠዋል ብለዋል።
ሽብርተኝነትን፣የሳይበር ወንጀልን፣ ህገወጥ የሰዎች ዝውውርን እና ሌሎች ድንበር ተሻጋሪ የወንጀል መረቦችን ለመከላከል የተቀናጀ ጥረት ማድረግ አስፈላጊ መሆኑንም አጽንኦት ሰጥተዋል ነው ያሉት።
ኢንተርፖል የኢትዮጵያን እና የአፍሪካን የፖሊስ ኃይሎች አቅም በመገንባት፣ሥልጠና በመስጠት እና የላቁ ቴክኖሎጂዎችን በማቅረብ ድጋፍ በሚያደርግበት ሁኔታ ላይም መወያየታቸውን ጨምረው ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ኢንተርፖል የሚጠቀምባቸውን ዓለም አቀፍ ቴክኖሎጂዎች እየተጠቀመች ነው ያሉት ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ፥ የዛሬው ውይይት ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን የታጠቀ ፖሊስን ለማጠናከር እና ስልጠና በመስጠት ግንኙነትን የበለጠ እንደሚያጎለብት አስታውቀዋል።
አክለውም ኢትዮጵያ በኢንተርፖል አባልነቷ ንቁ ተሳትፎ እያደረገች መሆኑን አንስተው፥ በቀጣይ በድርጅቱ ያላትን ተሳትፎ ለማጠናከር ጥረቷን አጠናክራ እንደምትቀጥል ጨምረው ተናግረዋል።
ሜጀር ጀነራል አል-ራይሲ በበኩላቸው፥ የተደራጁ ወንጀሎችን በመዋጋት ረገድ ኢንተርፖል ያለው ሚና ላይ ከኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ጋር መወያየታቸውን ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያ በድርጅቱ ውስጥ ከሰባት አስርት ዓመታት በላይ ያስቆጠረ የረጅም ጊዜ ተሳትፎ ያላት መሆኗን አንስተዋል፡፡
በተሳትፎዋ ኢትዮጵያ በተደራጁ ወንጀሎች፣በሳይበር ወንጀሎች እና በህገወጥ የሰዎች ዝውውር ላይ ወሳኝ ሚና እየተጫወተች እንደምትገኝ ገልጸዋል።