በአፋር ክልል የጤና መድህን አገልግሎት ተደራሽነትን የማስፋት ስራ ይከናወናል - ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ - ኢዜአ አማርኛ
በአፋር ክልል የጤና መድህን አገልግሎት ተደራሽነትን የማስፋት ስራ ይከናወናል - ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ
ሠመራ፣ሰኔ 27/2017(ኢዜአ)፡-በአፋር ክልል የጤና መድህን አገልግሎት ተደራሽነትን የማስፋት ስራ የሚከናወን መሆኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ ገለጹ።
የአፋር ክልል የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አገልግሎት የስራ ክንውን ላይ ያተኮረ የውይይት መድረክ ተካሂዷል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ እንደተናገሩት ባለፉት የለውጥ ዓመታት የጤና መድህን ሸፋንን ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቶ ሲሰራ ቆይቷል።
የአገልግሎቱን ጠቀሜታ ለአርብቶ አደሩ ማህበረሰብ ለማስገንዘብና የዘርፉን ተግዳሮቶች ለመቅረፍ በቅንጅት መሰራቱንም ተናግረዋል።
በቀጣይም ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት የጤና መድህን አገልግሎት ተደራሽነትን የማስፋት ስራ በልዩ ትኩረት የሚከናወን መሆኑንም ገልጸዋል።
የአፋር ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ያሲን ሐቢብ በበኩላቸው የጤና መድህን አገልግሎት ለበርካታ የክልሉ ዜጎች እፎይታን የሰጠ መሆኑን አብራርተዋል።
አገልግሎቱን ይበልጥ ለማስፋፋት ከባለድርሻ አካላት ጋር የተጀመረው ስራ የበለጠ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
በኢትዮጵያ ጤና መድህን አገልግሎት የአፋር ክልል ቅርንጫፍ ስራ አስኪያጅ ኢድሪስ መሐመድ (ዶ/ር) በበኩላቸው በክልሉ በጤና መድህን አገልግሎት በርካታ ሰዎችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል።
በዚህም በአገልግሎቱ 158 ሺህ 401 አባዎራዎችና እማዎራዎች እንዲሁም በቤተሰብ ደረጃ ደግሞ 902 ሺህ 891 ሰዎች ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ጤና መድህን አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ ወርቁ፤ በአገሪቱ የጤና መድህን አገልግሎትን የማስፋት ስራ ትኩረት ተሰጥቶት እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።
በተለይም አነስተኛ ገቢ ያላቸው ሰዎች ህክምና ለመስጠት የተጀመረው መርሃ ግብር ዛሬ ላይ በርካታ ሰዎችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል።
በውይይት መድረኩ ከክልል፣ ዞንና ወረዳ የመጡ የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።