"ኢትዮጵያዊ ዴሞክራሲ ፍለጋ" ታሪክ፣ፍልስፍና እና ባህላዊ እሴቶች ተጋምደው የቀረቡበት መጽሐፍ ነው - ኢዜአ አማርኛ
"ኢትዮጵያዊ ዴሞክራሲ ፍለጋ" ታሪክ፣ፍልስፍና እና ባህላዊ እሴቶች ተጋምደው የቀረቡበት መጽሐፍ ነው
አዲስ አበባ፤ሰኔ 27/2017(ኢዜአ)፦"ኢትዮጵያዊ ዴሞክራሲ ፍለጋ" ታሪክ፣ ፍልስፍና እና ባህላዊ እሴቶች ተጋምደው የቀረቡበት ድንቅ ስራ መሆኑ ተገለጸ።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጂጌ(ዶ/ር) የተጻፈ "ኢትዮጵያዊ ዴሞክራሲ ፍለጋ" መጽሐፍ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ራስ መኮንን አዳራሽ የምርቃት ሥነ-ስርዓት በመካሄድ ላይ ይገኛል።
በመጽሐፉ የምርቃት ሥነ-ስርዓት ላይ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ሃላፊና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ፣የፌዴራልና የክልሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሀላፊዎች እና ጥሪ የተደረገላችው እንግዶች ተገኝተዋል።
የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ፕሬዝዳንት ዛዲግ አብርሃ፣ የአዲስ አበባ እና የሀሮማያ ዩኒቨርሲቲዎች ምሁራን፤በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጂጌ(ዶ/ር) በተጻፈው "ኢትዮጵያዊ ዴሞክራሲ ፍለጋ" መጽሐፍ ላይ ገለጻ አድርገዋል።
በዚሁ ወቅት አቶ ዛዲግ አብርሃ እንደገለጹት "ኢትዮጵያዊ ዴሞክራሲ ፍለጋ" መጽሐፍ ሀገር በቀል የዴሞክራሲ እሴት የቀረበበት ነው።
በመጽሐፉም ኢትዮጵያ ከጥንት ታሪክ ጀምሮ የቅድመ አያቶች የዴሞክራሲ ልምምድ ባህላዊ እሴትና ፍልስፍና እንደነበራቸው የሚያመላክት መሆን ገልጸዋል።
መጽሐፉም ኢትዮጵያዊ ዴሞክራሲን በመዳሰስ ልዩ ያደርገዋል ያሉት አቶ ዛዲግ፥ ተስፋዬ በልጂጌ (ዶ/ር) ለቀጣዩ ትውልድ ትምህርት በሚሆን መልኩ መጽሐፉን እንዳዘጋጁት ተናግረዋል።
መጽሐፉ የሀገር በቀል ዕውቀትና ፍልስፍና ፋይዳዎች በሚገባ እንደተዳሰሱበት አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ ሀገር በቀል እሴት የታከለበት የዴሞክራሲ አሰራር ሥርዓትን ለመተግበር በምታደርገው ጥረትም ከፍተኛ ፋይዳ እንደሚኖረውም ገልጸዋል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አንጋፋ የፍልስፍና ምሁር ዳኛቸው አሰፋ (ዶ/ር)፥ "ኢትዮጵያዊ ዴሞክራሲ ፍለጋ" መጽሐፍ ጸሀፊ ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር) በመጽሐፋቸው የዴሞክራሲያዊ መርህ እኩልነትና ቅቡልነት በግልጽ ተመላክተውበታል ብለዋል።
በተለይም ታሪክ፣ ፍልስፍና፣ ባህላዊ እሴትና ሌሎች መሰረታዊ ሀሳቦች አጋምዶ የያዘ ድንቅ መጽሐፍ መሆኑን ገልጸዋል።
የሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ ምሁር ፕሮፌሰር ጀይላን ወሊ፥ ኢትዮጵያ የፍልስፍና እና ባህል ባለቤት ሀገር ናት ብለዋል።
በ"ኢትዮጵያዊ ዴሞክራሲ ፍለጋ" መጽሐፍ ላይ የኢትዮጵያ ድንቅ ባህላዊ የዴሞክራሲ እሴቶች ጥቅም ላይ አለመዋላቸውን በቁጭት እንደሚያትት ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ጥበብ የዴሞክራሲ መሰረት ነው ያሉት ፕሮፌሰሩ፥ልዮነትን እንደጸጋ በመቀበል የዴሞክራሲ ሥርዓትን መገንባት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
በመጽሐፉ ላይ ባህልና ሀገረሰብ እሴቶችን በማገናኘት የተካተቱበት መሆኑንም አንስተዋል።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር የሆኑት ተስፋዬ በልጂጌ(ዶ/ር) በማህበረሰባቸው ያዩት የዴሞክራሲ ልምምድ ባህላዊ እሴቶች "ኢትዮጵያዊ ዴሞክራሲ ፍለጋ" መጽሐፍን ለመፃፍ ያነሳሳቸው መሰረታዊ ጉዳይ መሆኑን አብራርተዋል።
የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ የግለሰብና የማህረሰብ ጉዳይ መሆኑን ያቀረቡበት መንገድም የሚደነቅ መሆኑን አብራርተዋል።
"ኢትዮጵያዊ ዴሞክራሲ ፍለጋ" መጽሐፍ በአራት ክፍሎች፣በ20 ምዕራፎችና በ454 ገፆች ተቀንብቦ ለአንባቢያን ቀርቧል።