ቀጥታ፡

በብዝሃ ዘርፍ ኢኮኖሚ እየተመዘገበ ያለውን የምጣኔ-ሀብት ዕድገትን ለማጽናት በሚደረገው ሂደት ድጋፋችንን እናጠናክራለን- የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት

አዲስ አበባ፤ሰኔ 27/2017(ኢዜአ)፦በብዝሃ ዘርፍ ኢኮኖሚ እየተመዘገበ ያለውን የምጣኔ-ሀብት ዕድገት ተከታታይነትን ለማፅናት በሚደረገው ሂደት  ድጋፋቸውን እንደሚያጠናክሩ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ገለፁ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ትናንት በምክር ቤቱ 42ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ተገኝተው በመንግስት የ2017 የሥራ አፈፃፀም ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በማብራሪያቸው ኢትዮጵያ ባለፋት ጥቂት ዓመታት በተለያዩ ዘርፎች የነበሩ ስብራቶቿን ለመጠገን የወሰደቻቸው የሪፎርም ስራዎች ተጨባጭ ውጤቶችን ማስመዝገባቸውን ገልጸዋል።

የግብርና ምርትና ምርታማነት መቀነስ፣ የንግድ ሚዛን መዛባት ፣የኢንዱስትሪ የማምረት አቅም ውስንነት፣ የውጭ ምንዛሬ እጥረትና የዕዳ ጫና ለአገራዊ ሪፎርሙ ገፊ ምክንያት መሆናቸውንም አንስተዋል።

የለውጡ መንግስት እነዚህን ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታት የወሰዳቸው የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርሞች አሁን ላይ የሚታይና የሚጨበጥ ውጤት  እያስመዘገበ መሆኑን በማስረጃ አስደግፈው አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ዕድገት ዋነኛ መሰረት ለሆነው ግብርና የተለየ ትኩረት መሰጠቱን በመናገር ሌሎች ዘርፎችም የምጣኔ-ሃብት ዕድገቱ መሰረት እንዲሆኑ መሰራቱን ነው ያብራሩት።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የምክር ቤት አባላት ኢትዮጵያ ዘላቂና አስተማማኝ የምጣኔ-ሀብት ዕድገት ለማስመዝገብ በብዝሃ ዘርፍ ላይ ትኩረት አድርጋ መስራቷ ትክክለኝ አቅጣጫ ነው ብለዋል።

የምክር ቤቱ አባል መስፍን ዳኜ ኢትዮጵያ በቱሪዝም ዘርፍ እምቅ ሃብት ቢኖራትም ዘርፉ ለምጣኔ ሃብት ዕድገቷ ጉልህ ሚና እንዳልነበረው አስታውሰዋል ።


 

ሌላው የምክር ቤት አባል አወቀ አምዛ (ዶ/ር)፤ ቀደም ሲል የኢትዮጵያ ምጣኔ-ሀብት ዕድገት በግብርና ላይ ጥገኛ እንደነበር አስታውሰዋል።

ይህም በዘርፉ የግብዓትና የምርታማነት እጥረት ሲያጋጥም ኢኮኖሚውም ይቀዛቀዝ እንደነበር በማስታወስ ለአብነት በቡና ወጪ ንግድ ላይ የነበረውን ውስንነት ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸውን ሀብቶቿን በመለየት ወደ ስራ መግባቷ በብዝሃ ዘርፍ ላይ የተመሰረተ ዕድገት ማስመዝገብ እንዳስቻላት የገለፁት ደግሞ የምክር ቤቱ አባል ሰሚራ የሱፍ ናቸው።


 

ሌላዋ የምክር ቤት አባል አረሬ ሞሲሳ ለተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋ ተጋላጭ በሆነው የግብርና ዘርፍ ላይ ብቻ ትኩረቱን ያደረገ ኢኮኖሚ አስተማማኝ መሰረት የለውም ብለዋል።

ይህን ተከትሎ መንግስት በብዝሃ ዘርፍ ላይ ያተኮረ አስተማማኝ የምጣኔ ሃብት ዕድገት እንዲመዘገብ የሰጠው ትኩረት ውጤት እያመጣ መሆኑን በመግለጽ።


 

በአገሪቱ እየተመዘገበ ያለውን ዘርፈ ብዙ የምጣኔ ሃብት ዕድገት የበለጠ ለማስቀጠል በሚደረገው ሂደት ድጋፋቸውን እንደሚያጠናክሩ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም