ቀጥታ፡

ህገወጥ ስደትን ለመከላከል ዓለም አቀፍ ትብብርን የማጠናከር ስራ ትኩረት ተሰጥቶታል

አዲስ አበባ፤ሰኔ 27/2017(ኢዜአ)፦ህገወጥ ስደትን ለመከላከል ዓለም አቀፍ ትብብርን የማጠናከር ስራ ትኩረት እንደተሰጠው በፍትህ ሚኒስቴር የብሄራዊ ፍልሰት ጥምረት ጽህፈት ቤት ሀላፊ አብርሃም አያሌው ገለጹ።

በኢትዮጵያ ህገወጥ ስደትን ለመከላከል ማህበረሰቡን ያሳተፉ በርካታ ተግባራት መከናወን ከጀመሩ አመታት ተቆጥረዋል።

በዚህ ረገድ ችግሩን ለመፍታት ታስቦ የተቋቋመውና የፌደራል ተቋማትን ያቀፈው የብሄራዊ ፍልሰት ጥምረት ጽህፈት ቤት በርካታ ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል፡፡

ጥምረቱ ስድስት አደረጃጀት ያለው ሲሆን የሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የስራና ክህሎት ሚኒስቴር፣ የትምህርት ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት፣ የኢትዮጵያ ዲያስፖራ አገልግሎት እና ፍትህ ሚኒስቴርን ያቀፈ ነው፡፡

በፍትህ ሚኒስቴር የብሄራዊ ፍልሰት ጥምረት ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አብርሃም አያሌው ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት፥የጥምረቱ መቋቋም መንግስት ለጉዳዩ የሰጠውን ትኩረት ያሳያል።

ህገወጥ የሰዎች ዝውውርን በቅንጅት ለመከላከልና ተያያዥ ችግሮችን ለመቅረፍ የተቋቋመው የብሄራዊ ፍልሰት ጥምረት ጽህፈት ቤት በርካታ ተግባራት እያከናወነ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ በህገ ወጥ ስደት የሚደርስን ወንጀል ለመከላከል የሚያስችል ልዩ ስትራቴጂና የፍልሰት ፖሊሲ በመቅረጽ ወደ ሚኒስትሮች ምክር ቤት መላኩን ተናግረዋል፡፡

ጥምረቱ ከተለያዩ አገራት ጋር በመቀናጀት ችግሩን ለመቅረፍ የሚያስችሉ በርካታ ተግባራትን በስፋት እያከናወነ እንደሚገኝ ሃላፊው አስታውቀዋል፡፡

ካለው ችግር አኳያ ብዙ መስራት እንደሚጠበቅ ያነሱት የጽህፈት ቤት ሀላፊው በተለይ ቅንጅት ላይ በተጠናከረ ሁኔታ ለመስራት የሚያስችል መመሪያ መዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡

መመሪያው ሀላፊነታቸውን በአግባቡ የማይወጡ የጥምረቱ አባል ተቋማት ተጠያቂ የሚሆኑበትን አሰራር በመያዙ ትብብሩን ይበልጥ ለማጠናከር ትልቅ አቅም ይሆናል ብለዋል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ከዓለም አቀፍ አገራት ጋር ያለውን ትብብር የማጠናከር ስራ በትኩረት እንደሚሰራ አስታውቀዋል፡፡

ትብብሩ ዜጎች በሚኖሩበት አገር በአግባቡ እንዲያዙና ክብር በተሞላበት ሁኔታ ወደ አገራቸው እንዲመለሱ፤ ወንጀሉን ለመከላከል በቅንጅት ለመስራት እንዲሁም ወንጀለኞችን በጋራ አድኖ ለመያዝ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም