"ኢትዮጵያዊ ዴሞክራሲ ፍለጋ" ታሪክ፣ ፍልስፍና እና ባህላዊ እሴቶች አጋምደው የቀረቡብት መጽሐፍ ነው - የአዲስ አበባና የሀሮማያ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን - ኢዜአ አማርኛ
"ኢትዮጵያዊ ዴሞክራሲ ፍለጋ" ታሪክ፣ ፍልስፍና እና ባህላዊ እሴቶች አጋምደው የቀረቡብት መጽሐፍ ነው - የአዲስ አበባና የሀሮማያ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 27/2017(ኢዜአ)፦"ኢትዮጵያዊ ዴሞክራሲ ፍለጋ" ታሪክ፣ ፍልስፍና እና ባህላዊ እሴቶች ተጋምደው የቀረቡበት ድንቅ ስራ መሆኑን የአዲስ አበባና የሀሮማያ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ገለጹ።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጂጌ(ዶ/ር) የተጻፈ "ኢትዮጵያዊ ዴሞክራሲ ፍለጋ" መጽሐፍ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ራስ መኮንን አዳራሽ የምርቃት ሥነ-ስርዓት በመካሄድ ላይ ይገኛል።
በመጽሐፉ የምርቃት ሥነ-ስርዓት ላይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ሃላፊና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ፣ የፌዴራልና የክልሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሀላፊዎች እና ጥሪ የተደረገላችው እንግዶች ተገኝተዋል።
የአዲስ አበባና የሀሮማያ ዩኒቨርሲቲዎች ምሁራን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጂጌ(ዶ/ር) በተጻፈ "ኢትዮጵያዊ ዴሞክራሲ ፍለጋ" መጽሐፍ ላይ ገለጻ አድርገዋል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አንጋፋ የፍልስፍና ምሁር ዳኛቸው አሰፋ (ዶ/ር)፥ "ኢትዮጵያዊ ዴሞክራሲ ፍለጋ" መጽሐፍ ጸሀፊ ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር) በመጽሐፋቸው የዴሞክራሲያዊ መርህ እኩልነትና ቅቡልነት በግልጽ ተመላክተውበታል ብለዋል።
በተለይም ታሪክ፣ ፍልስፍና፣ ባህላዊ እሴትና ሌሎች መሰረታዊ ሀሳቦችን አጋምዶ የያዘ ድንቅ መጽሐፍ መሆኑን ገልጸዋል።
የሀሮማያ ዩኒቨርሲቲ ምሁር ፕሮፌሰር ጀይላን ወሊ፥ ኢትዮጵያ የፍልስፍና እና ባህል ባለቤት ሀገር ናት ብለዋል።
በ"ኢትዮጵያዊ ዴሞክራሲ ፍለጋ" መጽሐፍ ላይ የኢትዮጵያ ድንቅ ባህላዊ የዴሞክራሲ እሴቶች ጥቅም ላይ አለመዋላቸውን በቁጭት እንደሚያትት ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ጥበብ የዴሞክራሲ መሰረት ነው ያሉት ፕሮፌሰሩ፥ ልዮነትን እንደጸጋ በመቀበል የዴሞክራሲ ሥርዓትን መገንባት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
በመጽሐፉ ላይ ባህልና ሀገረሰብ እሴቶችን በማገናኘት የተከተበበት መሆኑንም አንስተዋል።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጂጌ(ዶ/ር) በማህበረሰባቸው ያዩት የዴሞክራሲ ልምምድ ባህላዊ እሴቶች "ኢትዮጵያዊ ዴሞክራሲ ፍለጋ" መጽሐፍን ለመፃፍ ያነሳሳቸው መሰረታዊ ጉዳይ መሆኑን አብራርተዋል።
የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ የግለሰብና የማህረሰብ ጉዳይ መሆኑን ያቀረቡበት መንገድም የሚደነቅ መሆኑን አብራርተዋል።
"ኢትዮጵያዊ ዴሞክራሲ ፍለጋ" መጽሐፍ በአራት ክፍሎች፣ በ20 ምዕራፎችና በ454 ገፆች ተቀንብቦ ለአንባቢያን ቀርቧል።